የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመደገፍና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመደገፍና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመደገፍና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ መሆኑን የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ በቀለ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ወደ ሙሉ ትግበራ ከመግባቱ በፊት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል።
በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የውጭ ኢንቨስትመንትን መደገፍ የሚያስችሉ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ በቀለ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ያለውን የመሪነት ሚና በላቀ መልኩ ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በዘርፉ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ የሚያስችል ዝግጅትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በዚህ ረገድ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ጥናት ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ወደ ትግበራ መገባቱንም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የባንክ ሴክተሩን ጨምሮ ሌሎችም ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እየተደረጉ በመሆኑ የባንኩን ዓለም አቀፍ አገልግሎት ለማሳካት በመሠረተ ልማት፣ በሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ከእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለፈ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመሳብ ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስትመንቶችን ለመደገፍ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት 135 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የተሳካለት ሲሆን፤ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን 1 ነጥብ 17 ትሪሊየን ብር እንዲሁም የደንበኞቹ ቁጥር ከ45 ሚሊየን በላይ መድረሱ ይታወቃል።