የቦይንግ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት በመጪው ጥቅምት ሥራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የቦይንግ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት በመጪው ጥቅምት ሥራ ይጀምራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የቦይንግ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት በመጪው ጥቅምት ሥራ እንደሚጀምር የኩባንያው የአፍሪካ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሄኖክ ተፈራ ገለጹ።
የአሜሪካው ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ በቅርቡ የአፍሪካ ዋና ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ለመክፈት በሂደት ላይ እንደነበር መግለጹ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በመጪው ጥቅምት የኩባንያው ጽሕፈት ቤት ሥራውን በይፋ እንደሚጀምር ነው የቦይንግ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሄኖክ ተፈራ ለኢዜአ የገለጹት።
ቦይንግ የአፍሪካ ዋና ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ የከፈተው ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ስኬታማ ሥራ ከግምት በማስገባትና አገሪቱ የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ተከትሎ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቦይንግ ኩባንያ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ መከፈቱ ቦይንግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያሉትን ትብብሮች ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋት እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን የጽሕፈት ቤቱ መከፈት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከልነቷን አጠናክራ ለማስቀጠል ተጨማሪ እድል እንደሚፍጥርላትም ነው ያብራሩት።
በቀጣይ ቦይንግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተመተባበር በተለይም የአውሮፕላን ክፍሎች/እቃዎች በጋራ ለማምረት የሚያስችል ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።