የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አመራር አባላትና ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አመራር አባላትና ሰራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
አዳማ ፤ ነሐሴ 20/2016 (ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አመራር አባላትና ሰራተኞች በአዳማ ከተማ አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።
ጽህፈት ቤቱ ከኦሮሚያ ክልል ታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ነው ዛሬ በአዳማ ከተማ ጎሮ ወረዳ ጮቆኑ ተራራ ላይ ችግኝ የተከሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የህዳሴ ግድብ ረጅም አገልግሎት እንዲሰጥ ትልቅ አስታዋጽኦ ያበረክታል።
በዚሁ መነሻነት የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አመራር አባላትና ሰራተኞች ባለፉት ዓመታት በተከታታይ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ እየተሳተፉ ነው ብለዋል።
ግድቡ በጎርፍ ምክንያት በደለል እንዳይሞላ የአካባቢያችን ብሎሞ የምድራችንን ተፈጥሯዊ ይዘት ለመመለስ በችግኝ ተከላውና እንክብካቤው የሁሉም ዜጋ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
አረንጓዴ አሻራ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህዝብ የጋራ ተሳትፎ ፍሬያማ እየሆነ መምጣቱም የሚያኮራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ በበኩላቸው ማስተባባሪያው በችግኝ ተከላው እየተሳተፈ መሆኑን አስታውሰዋል።
ማስተባበሪያ ካለው ሃላፊነት ባሻገር ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችልና የአካባቢ ስነ-ምህዳር እንዲጠበቅ ሁሉም ሰው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲሳተፍ የማስገንዝብ ስራ መስራቱንም ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራው መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ከመፍታት ባሻገር ለበርካቶች የስራ እድል በመፍጠር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ህዝባችን ተባባሪነቱን ማሳየትና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ሲሉም አክለዋል።