በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፓሪስ አቀባበል ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፓሪስ አቀባበል ተደረገለት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016 (ኢዜአ):- በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፓሪስ አቀባበል ተደርጎለታል።
ልዑካን ቡድኑ ዛሬ ማለዳ ቻርልስ ደጎል ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በአገሪቷ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት አቀባበል እንዳደረጉለት የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል።
17ኛው የፓራምፒክ ጨዋታዎች ከነሐሴ 22 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ከ184 አገራት የተወጣጡ 4 ሺህ 400 አትሌቶች በ22 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ጾታዎች ስድስት ተወዳዳሪዎችን ታሳትፋለች።
ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በ1 የወርቅ ሜዳሊያ 59ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።