ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ክለብ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016 (ኢዜአ)፡- በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም እግር ኳስ ክለብ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያከናውናል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የማጣሪያ ውድድር ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል።

ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ እየተሳተፈ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም እግር ኳስ ክለብ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ በአበበ በቂላ ስታዲየም ያደርጋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ 1 ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በማሸነፍ ምድቡን በመሪነት ማጠናቀቁ ይታወቃል።

ንግድ ባንክ በሶስቱ ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።

አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ አምስት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራች ትገኛለች።

ተጋጣሚው ካዌምፔ ሙስሊም እግር ኳስ ክለብ በምድብ 2 ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፎ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ቡድኑ በሶስቱ ጨዋታዎች 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 3 ግቦች ተቆጥረውበታል።

በምድቡ የጅቡቲውን ፋድ 10 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት የረታበት ጨዋታ በውድድሩ የተመዘገበ ትልቁ ውጤት ነው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በፍጻሜው ከታንዛንያው ሲምባ ኩዊንስ እና ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

ሲምባ ኩዊንስና ኬንያው ፖሊስ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ዛሬ ከረፋዱ 5 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደርጋሉ።

ሲምባ በምድብ 2 በሰባት ነጥብ አንደኛ፣ ኬንያ ፖሊስ በምድብ 1 በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።

የፍጻሜው ጨዋታ ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ያሸነፈው ክለብ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዞንን ወክሎ በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም