አዲስ አበባ በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ አደባባይ ተሰየመላት - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ አደባባይ ተሰየመላት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2016 (ኢዜአ):- በጀርመን የላይፕዚግ ከተማ በአዲስ አበባ የተሰየመው አደባባይ በሊፕዚግ እና በአዲስ አበባ መካከል የእህትማማች ከተማ አጋርነትን እንደሚያጠናክረው ተገለጸ፡፡
በጀርመን የላይፕዚግ ከተማ በአዲስ አበባ የተሰየመ አደባባይ በሊፕዚግ እና በአዲስ አበባ መካከል የእህትማማች ከተማ አጋርነት 20ኛ ዓመት የማክበር ስነ-ስርዓት ላይ እ.ኤ.አ ነሀሴ 23/2024 ተመርቋል።
በታሪካዊው የላይፕዚግ እምብርት ላይ የተካሄደው ስነ-ስርዓት ላይ የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካዮች ፣ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮች፣ የላይፕዚግ ባለስልጣናትና በአካባቢው ያሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
አደባባዩ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑንም የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግ በአፅንኦት ገልፀዋል።
የአዲስ አበባን ከንቲባ ወክለው የተገኙት የከንቲባ አማካሪ አቶ አሻግሬ ገብረወልድ የአደባባዩ መመረቅ ለሁለቱ ከተሞች እና ለሁለቱ ሀገራት ዘለቄታዊው ግንኙነት የላቀ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአደባባዩ መሰየም አጋርነትንና የጋራ ታሪክን ከመዘከር ባለፈ በቀጣይ ለሚደረጉ የሁለትዮሽ ትብብሮች መንገድ የሚከፍት መሆኑን አመልክተዋል።
ዝግጅቱ ሁለቱ ከተሞች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና የጋራ ዕድገትን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑንና አዲስ አበባም አጋርነቱን ለማስፋት ቁርጠኝነቷን ማረጋገጧን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።