በመጪው የበዓል ወቅት የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከ82 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ግዥ ተፈጽሟል-የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2016 (ኢዜአ):- በመጪው የበዓል ወቅት የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከ82 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ግዥ መፈጸሙን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት አስታወቀ፡፡

በተጨማሪም የ200 ሺህ ኩንታል ስኳር ግዢ መፈጸሙንና በቀጣይ ሳምንት ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ እንደሚከናወንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሺመቤት ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ተቋሙ ከተሰጡት በርካታ ተግባራት መካከል የአቅርቦት ክፍተቶችን ለሟሟላትና ገበያን ለማረጋጋት የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለሽያጭ ማቅረብ አንዱ ነው፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎም ሰውሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ድርጅቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም ከ82 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 54 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ የሱፍ ዘይት ሲሆን፤ 28 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትሩ ደግሞ ፓልም የምግብ ዘይት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዘይት ምርቱን ከመጪው የበዓል ወቅት ቀደም ብሎ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በበዓል ወቅት የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የ200 ሺህ ኩንታል ስኳር በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የውጭ ሀገር ግዥ መፈጸሙን ገልጸው፤ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደሚጀምር ነው የተናገሩት፡፡

ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመሰረታዊ ሸቀጦች በተጨማሪ፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የህንጻ መሣሪያዎች፣ የጽህፈት መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ በ83 ቅርንጫፎቹ አማካኝነት ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ድርጅቱ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ 585 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት ችሏል ነው ያሉት፡፡

አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም