በተለያዩ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ዘላቂ የከተሞች እድገትና ትስስርን የሚያሳልጥ ነው-ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2016(ኢዜአ)፦ በተለያዩ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ዘላቂ የከተሞች እድገትና ትስስርን የሚያሳልጥ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።   

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የኢትዮጵያን ከተሞች ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የከተማ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከዚህም ውስጥ የኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ሲሆን፤ የኮሪደር ልማት ስራዎች በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በ31 ከተሞች እየተከናወኑ ነው፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ከተሞች የሰፋው የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን ለኑሮ ተስማሚ የሚያደርግ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተሞች ዘላቂ የሆነ ፕላን እንዲኖራቸውና በየጊዜው ለማስፋት ሲባል የማፍረስ ሂደቶችን የሚያስቀር መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

በተጨማሪም ዘመናዊ እና ስማርት ከተሞችን በመፍጠር ዘላቂ የከተሞች እድገትና ትስስርን የሚያሳልጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ከተሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተሞች በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉ ከማድረጉም ባሻገር ንጹህ እና አረንጓዴ ገጽታ እንዲላበሱ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በከተሞች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች የልማት ስራ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ከተሞችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች  እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችም የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ዜጎች በልማት ስራዎች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም