ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚደረግ ተጋድሎ

አለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ውስጥ መገኘቷን ተከትሎ የታላላቅ አገራት መሪዎችን ጨምሮ ባለሙያዎች መፍትሄ ለማምጣት ደፋ ቀና እንዲሉ አስገድዷቸዋል።

ሰዎች የሚከተሏቸው ያልተገቡ የአኗኗ ዘይቤዎች ተፈጥሮን እያራቆቱ መሄዳቸው እየዋለ ሲያድር በየፈርጁ መልሶ ራሳቸውን ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል።

ቀውሱ ድሃና ሃብታም የሚባሉ ሃገራትን ሳይለይ የጥፋት በትሩን ሁሉም ላይ አሳርፏል።

የአየር ንብረት ለውጡ ቀድሞ የበላቸውም ሆነ ቀጣዩ ቀውስ የሚያሰጋቸው የተለያዩ አገራት ችግሩን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራትና አጀንዳቸው ብሎም የፖሊሲያቸው አካል አድርገው መንቀሳቀስ  ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።

ሁሉም በየፊናቸው የዓለም ስጋት ለሆነው ቀውስ መፍትሔ የሚሉትን ተግባር በማከናወን ላይ ናቸው።

ለአለም አየር ንብረት ለውጥ ያደጉ አገራት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ቢሆንም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ግን ታዳጊ አገራት ናቸው።

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍና ተያያዥ ችግሮች በየጊዜው እየተፈተነች ትገኛለች።

በተለይም ከፍተኛ የካርበን መጠን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ለአየር ንብረት ተፅእኖ ያላት አስተዋጽኦ አራት በመቶ ብቻ ቢሆንም በቀውሱ ግን ዋነኛዋ ገፈት ቀማሽ እሷ ራሷ ሆናለች።

ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ባለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ተጋላጭ በመሆን በተደጋጋሚ ለሚከሰት የድርቅ ፣የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ መሆኗ አልቀረም።

ኢትዮጵያ ይህንን ምስል ለመለወጥና ዓለም አቀፍ ችግሩን ለመከላከልና ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት መርኃ ግብር ነድፋ ተግባራዊ እንቀስቃሴዎችን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።

በዚህ ረገድ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በተቀናጀ ሁኔታ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተጠቃሽ ነው።

ለአረንጓዴ አሻራ መነሻ የሆኑ ገፊ ምክንያቶች ምን ነበሩ

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የስነ-ምህዳር መጎሳቆል ለመርኃ ግብሩ መጀመር አንዱ ገፊ ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያ ካላት 112 ሚሊዮን ሄክታር የቆዳ ስፋት 54 ሚሊዮን ሄክታሩ በተለያየ ደረጃ የተጎሳቆለ መሆኑን ጥናቶችን ጠቅሰው ተናግረዋል ።

በሌላ በኩል በዓመት የሚጨፈጨፈው ከ 92 ሺ ሄክታር በላይ ደን የስነ-ምህዳር መዛባቱን አባብሶታል።

ይህም በአገሪቷ ከፍተኛ የስነ-ምህዳር መጎሳቆልና የደን መመናመን እንዲፈጠር ማድረጉን ነው ዶክተር አደፍርስ የሚገልጹት።

በእነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ለተደጋጋሚ የድርቅ፣ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተጋላጭ ከመሆን ባለፈ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ በ2011 ዓ-ም ሲጀመር የተዛባውን ስነ-ምህዳር ማሻሻልና ኢኮኖሚውን መደገፍን ዓላማ አድርጎ መነሳቱን ነው አስተባባሪው የሚያስታውሱት።

ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቦታ መረጣና ችግኝ ማፍላትን ጨምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት አስቀድሞ በመጀመሩ ውጤት መገኘቱን  ነው ያነሱት።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ እንደሚሉት፣ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን የምትተገብረው ለትውልድ የሚተርፍ ጸጋን ለማውረስ ነው።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባትና ከተረጂነት ለመውጣት የአካባቢን ስነ-ምህዳር መጠበቅና መንከባከብ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ገቢራዊ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና መጫወቱን ነው ያብራሩት።

መርኃ ግብሩ የከተማ ልማትን የቱሪዝምና ኢንዱስትሪ ዘርፉን ቀጥተኛ ተጠቃሚ በማድረግ ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፍ አገራዊ እሳቤ ነውም ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረጉ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የህዝቡን ማህበራዊ ትስስር የበለጠ ያጠናከሩ እንደነበሩም አስታውቀዋል።

የደን ማልማት ሥራዎችም በአየር ንብረት ሥርዓቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ  ከማምጣት ባሻገር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን እንዲጨምርና ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን የካርበን ክምችት እንዲኖር ማስቻሉንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡  

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ምን ውጤቶችን እያስገኘ ነው

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 23 በመቶ ከፍ እንዲል አድርገዋል።

በእርሻ ቦታዎች አካባቢ የሚተከሉ ዛፎች አፈርን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍ ያጠቃቸው የነበሩ ክልሎች ላይ የውሃ መጠንን በመጨመርና የመኖ አቅርቦትን በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።

2016 ዓ.ም. ''የምትተክል ሀገር፤ የሚያጸና ትውልድ!'' በሚል መሪ ሀሳብ በ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል መርኃ ግብር እንደቀጠለ ነው።

በዚህም እስካሁን 6 ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር አረጋግጧል።

መርኃ ግብሩ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ ነሃሴ 17 ቀን 2016 በተከናወነው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ከ 615 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል።

ለተከላው በተለይም የአካባቢ መራቆት ይታይባቸው የነበሩ 8 ሺህ ተፋሰሶች የቦታ መጠነ-ልኬትና የካርታ ዝግጅት ቀደም ብሎ መከናወኑ ይታወቃል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፤  በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በሁሉም ረገድ የአፈርና የስነ-ምኅዳር ሁኔታን ታሳቢ ያደረጉ ችግኞች የሚተከሉ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል 56 በመቶ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያገለግሉ ናቸው።

በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች የጽቅደት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና የህብረተሰቡም ችግኞችን የመንከባከብ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን በበጎ አንስተዋል ።

ትውልዱ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እያሳየ ያለው ተሳትፎና ተነሳሽነት ለአለም ፈተና መፍትሄ የሚሰጥ የዘመኑ አርበኝነት ተምሳሌትና የአለም ችግር መፍቻ ቁልፍ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

አለምን በብዙ እየፈተነ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ተጋድሎ ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆንና የኢትዮጵያን ጥረት ለመደገፍ የሚያነሳሳ ተግባር መሆኑ እሙን ነው።

በዘንድሮ የአረንጓዴ  አሻራ መርሃ-ግብር በተቀናጀና በተናበበ መልኩ መከናወኑ ደግሞ አገሪቷ በቀጣይ ካርቦን በመሸጥ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር የሚፈለገው ግብ እንዲመታ ከተፈለገም  በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ምእራባውያን አገራት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገራት ጋር በቅርበት መስራት የግድ  ይላቸዋል፡፡

የዘርፋ ምሁራንም "ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ሌሎች አገራትን የሚታደግ ስራ እየሰራች በመሆኑ ለምታበረክተው አስተዋጽኦ ተገቢው ዕወቅና ሊቸራት እንዲሁም ገንዘብን ጨምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል "እያሉ ናቸዉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንድ ጀንበር የ600 ሚሊዮን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር መጠናቀቁን ሲያበስሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ''ያሰብነውን ሳናሳካ ጀንበር የምትጠልቅብን አይደለንም፣ በአንድ ጀንበር 615 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ችለናል''ነው ያሉት።

ሁሉም ከተባበረና ለአንድ ዓላማ በጋራ ከቆመ የማይቻል ነገር አለመኖሩን ከኛ ከኢትዮጰያውያን በላይ ማን ሊረዳ ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላው ህጻናት ተስፋቸውን ተክለዋል፣ወጣቶች ጽናታቸውን አሳይተዋል፣ አረጋውያን ውርስ አኑረዋል፣ ኢትዮጰያውያን በአጠቃላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በነቂስ ወጥተው የማይደበዝዝና የማይጠፋ አሻራቸውን ለመጪው ትውልድ አኑረዋል።

በአንድ ቀኑ የጋራ ርብርብ ከ29 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በ318 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ በጂኦስፓሺያል በተደገፈ መረጃ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ይህም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚደረግ ተጋድሎ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት የሰጡት።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም