በዞኑ በመሬት መንሸራተት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሙ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በመሬት መንሸራተት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሙ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው
ጎንደር፤ ነሐሴ 19/2016(ኢዜአ)፡- በሰሜን ጎንደር ዞን ሶስት ወረዳዎች በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በአደጋው የሰዎች ህይወት ማለፉንና ህይወት የመታደጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
በጠለምት ወረዳ በአደጋው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 8 ሰዎችም በአካባቢው የጤና ተቋማት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በወረዳዎቹ በደረሰው አደጋ የሰው ህይወት ከማለፉም ሌላ ከ2 ሺህ 700 በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አደጋው የደረሰው በዞኑ በጠለምት፣ በአዲአርቃይና በየዳ ወረዳዎች በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡
ከተለያዩ የመንግስት አካላት ተውጣጥቶ የተቋቋመው ግብረ ሃይል በተለይ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰበት የጠለምት ወረዳ በመገኘት ህብረተሰቡን የማረጋጋትና የአደጋውን መጠን መረጃ የማሰባሰብ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች የእለት ምግብ እርዳታን ጨምሮ የመጠለያ አገልግሎት እንዲያገኙ ግብረ ሃይሉ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር ሰፊ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በጠለምት ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 8 ሰዎችም በአካባቢው የጤና ተቋማት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ሰዎችን የመታደጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡
በመሬት መንሸራተት አደጋው በሶስቱ ወረዳዎች በ1 ሺ 775 ሄክታር ላይ የተዘራ ሰብል መውደሙን ጠቅሰው፤ 48 መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፤ 2ሺህ 700 ነዋሪዎችም ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አስረድተዋል፡፡
የዞኑ አስተዳደርና ህብረተሰቡ በወረዳዎቹ በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ በተጎዱ ዜጎች ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማቸው ጠቁመው ፤የክልሉ መንግስት አስቸኳይ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ መቅረቡንም አስታውቀዋል፡፡
አካባቢዎቹ በተደጋጋሚ ድርቅ ደርሶባቸው የቆዩ መሆናቸውን ያስታወሱት ሃላፊው በመላ አገሪቱ የሚገኙ ዜጎች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡