በበጀት ዓመቱ እመርታ የታየበት ገቢ ምርትን የመተካት ሥራ ተሰርቷል - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ እመርታ የታየበት ገቢ ምርትን የመተካት ሥራ ተሰርቷል - አቶ መላኩ አለበል
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በ2016 የበጀት ዓመት ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ሥራ አመርቂ ዕድገት የታየበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2017 ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው ።
በውይይቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በ2016 በጀት ዓመት ሚኒስቴሩ እንደ ሀገር በዘርፉ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ያከናወናቸው ተግባራት ጥሩ አፈፃፀም የታየባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።
በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካቱ ረገድ የንግድ ሚዛኑን ለማጣጣም የተሰራው ሥራ ከፍ ያለ አፈፃፀም የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በሀገሪቷ በሁሉም ክልሎች ያሉ ፀጋዎችን በማጤንና ሊመረቱ የሚችሉ ተኪ ምርቶችን ለይቶ በማምረት የመጣ ውጤት እንደሆነ ነው የገለፁት ።
የአምራች ኢንዱስትሪውን የገበያ ድርሻ የማሳደግ ሥራውም እንዲሁ ስኬታማ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ የኢንዱስትሪውን የገበያ ድርሻ በ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ውስጥ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በበጀት ዓመት 39 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ነው ያስረዱት።
አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት፣ የወጪ ምርትን በማሳደግ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንዲችል በማድረግ ረገድም ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የገለፁት።
በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ በ2017 ለሚከናወኑ ትላልቅ ተግባራት መሰረት የሆኑ አመርቂ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ የሚጠይቁ ሥራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል ብለዋል።
በሚኒስትሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን አባይ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በተደረገው ንቅናቄ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥና ዕድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በምግብና መጠጥ ዘርፎች በአጠቃላይ 96 ስትራቴጂክ ተኪ ምርቶች ተለይተው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንዲመሩ በመደረጉ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
በ2013 በጀት ዓመት ከውጭ ይገቡ የነበሩና በሀገር ውስጥ ምርት የተተኩ ምርቶች ግምታቸው 248 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያወሱት አቶ ጥላሁን፤ በ2016 ይህንን አሃዝ ወደ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ እንደተቻለ በማንሳት።
በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አማካይ ሀገራዊ ዕድገትም 10 ነጥብ 2 በመቶ ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልፀዋል።
እስከ 2022 ዓ.ም ይህ አማካይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገራዊ እድገቱ ወደ 22 ነጥብ 08 በመቶ ከፍ እንዲል የ10 ዓመት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በ2017ዓ.ም 12 ነጥብ 08 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ክልሉ ካለው የመሬት ጥበትና የሥራ ፈላጊዎች ብዛት አኳያ አምራች ኢንዱስትሪውን ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ 21 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸው፤ የአሰራር ሥርዓቶችን የማሻሻልና ሌሎች ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱ ሙክታር በበኩላቸው በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተኪ ምርቶች፣ በአዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያን ምቹ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑበት ዓመት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ አብዱ ገለፃ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ በከተማ አስተዳደሩ 17 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ከዚህ በፊት ተዘግተው የነበሩ ዘጠኝ ከፍተኛ እንዲሁም 14 መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ችለናል ብለዋል።
በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና የተጠሪ ተቋማት የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።