ኢትዮጵያ ቡና የካፍ ኮንፌዴሬሽን የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቡና የካፍ ኮንፌዴሬሽን የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቡና በ2024/25 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከኬንያው ኬንያ ፖሊስ ጋር ዛሬ ያከናውናል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ አበበ በቂላ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
ቡድኖቹ ናይሮቢ ላይ ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው ይታወቃል።
ናሚቢያዊው ምዌሺትሳማ ኔጎንጎ ናፍታል የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ኢትዮጵያ ቡና በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛው ዙር ከግብጹ ዛማሌክ ጋር ይጫወታል።
ዛማሌክ የወቅቱ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ባለቤት ነው።
ኢትዮጵያ ቡና በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
በተያያዘም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን የወከለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትናንት ባደረገው የመልስ ጨዋታ ከዩጋንዳው ቪላ ክለብ ጋር 1 ለ 1 አቻ ወጥቷል።
ውጤቱን ተከትሎም ንግድ ባንክ በአጠቃላይ ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።