ቀጥታ፡

ወጣቶች በሰላም ግንባታና በልማት ሥራዎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ ወጣቶች በሰላም ግንባታና በልማት ሥራዎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ  የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለፁ።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማኅበር ጋር በመተባበር "ወጣቶች በአገር ሰላምና አካባቢ ጥበቃ ላይ  ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ኃሳብ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ለሦስት ቀና የሚቆይ ፎረም ማካሄድ ጀምሯል። 

በፎረሙ ከፍተኛ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ፤ የአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት  ሊረጋገጥ የሚችለው ወጣቱ አምራች ኃይል በአገሪቱ የልማትና የሰላም ጉዳይ ላይ በንቃት ሲሳተፍ ነው ብለዋል።

ለዚህም መንግሥት በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በርካታ ወጣት ያለባት አገር እንደመሆኗ መንግሥት በሚሰራቸው ሥራዎች ብቻ ወጣቶች በሚፈለገው ደረጃ በሰላምና በልማት ላይ ማሳተፍ አዳጋች መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ የሲቪል ድርጅቶች ተሳትፎ ያስፈልጋል ነው ያሉት።  

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ሰላም ማኅበር፤ ወጣቶች በአገር ሰላም ጉዳይና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ለማሳደግ ፎረም መዘጋጀቱ የሚበረታታና በቀጣይም ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። 

ሁሉም ወጣት  በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ  ብሎም በአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ጫላ አሰፋ በበኩሉ ፎረሙ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ገልጾ በመድረኩም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ከ250 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ብሏል። 

በመድረኩም በሰላም ጉዳይና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ያሉ ተግዳሮቶች ለመፍታት ወጣቶች መወጣት በሚገባቸው ሚና ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ትኩረት ይደረጋልም ነው ያለው። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም