በዲጂታል ቴክኖሎጂ ራሳችንን ወደ ምንፈልግበት ደረጃ ለማሳደግ የሚረዱ ክህሎቶችን እያገኘን ነው - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል ቴክኖሎጂ ራሳችንን ወደ ምንፈልግበት ደረጃ ለማሳደግ የሚረዱ ክህሎቶችን እያገኘን ነው - ወጣቶች
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ራሳቸውን ወደሚፈልጉበት ደረጃ ለማሳደግ የሚረዱ ክህሎቶችን እያገኙ መሆናቸውን በሲዳማ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ወጣቶች ገለጹ ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ አምስት ሚሊዮን ኮደርስን ለማሰልጠን በተዘረጋው መርሀ ግብር አማካኝነት በክልሉ የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች ሥልጠናውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህረፍት ላይ ላሉ ተማሪዎችና ወጣት ባለሞያዎች፣ ራሳቸውን በዕውቀት በመገንባት በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር ለሚሹ ሁሉ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ፕሮጀክት ቀዳሚ ሊያደርጋቸው መሰናዳቱን ገልፀዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የክህሎት አበልፃጊዎች፣ አሣዳጊዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን ፕሮጀክት እና እንቅስቃሴዎቹን እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
በዚህም መሰረት የሲዳማ ክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲም ሀዋሳ በሚገኘው ማዕከሉ ወጣቶችን እያሰለጠነ ይገኛል።
በማዕከሉ ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ወጣቶች እንደገለፁት፤ ስልጠናው በዘርፉ ያላቸውን ክህሎት ለማሳደግ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
በዚህም በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ ራሳቸውን ወደ ሚፈልጉበት የዕድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያግዟቸውን ክህሎቶች ከሥልጠናው እያገኙ መሆናቸውን ነው ለኢዜአ የገለጹት።
የኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የ4ኛ ዓመት ተማሪ እሱባለው በለጠ፤ የኮምፒውተር ተማሪ በመሆኔ ብዙ ክህሎቶች ሊኖሩኝ ይገባል ብሏል።
''የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና በውስጡ ከያዛቸው ካሪኩለምና ፓኬጆች አኳያ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶችን የያዘ ወሳኝ ዕድል ነው'' ሲል ነው የተናገረው።
በሥልጠናው ካሉት የኮርስ ምርጫዎች ውስጥ ዳታ ሳይንስን በመምረጥ እየተከታተለ እንደሚገኝም ጠቅሷል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሶሊያና አያሌው በበኩሏ ዌብ ሳይቶችን ማበልፀግ ላይ ብዙ የመስራት ዓላማ እንዳላት ተናግራለች።
ሥልጠናው ወደፊት የምታስበውን ለማሳካት የሚያስችላትን ክህሎት በቀላል መንገድ ለመረዳት የሚያስችላት መሆኑን ገልፃለች።
''እንዲህ አይነት ሥልጠናዎችን በግል ለማግኘት ብዙ ገንዘብና ጊዜን ይጠይቃል'' ያለችው ተማሪ ሶሊያና ''አሁን ላይ ጊዜያችንን በሚቆጥብ መልኩ በቀላሉ ለመሰልጠን የሚያስችል ዕድልና አጋጣሚ ተፈጥሮልናል'' ብላለች።
ስልጠናው በኦንላይን በመሆኑ በፈለኩበት ጊዜ ለመሰልጠን አስችሎኛል ያለው ደግሞ በሃዋሳ የቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪው አንተነህ ማስረሻ ነው።
''ስልጠናው ሕይወታችንን ቀላል የሚያደርጉና ችግሮቻችንን የሚፈቱ መተግበሪያዎችን ለመስራት እንድንጥር አነሳስቶኛል'' ብሏል፡፡
የሲዳማ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ በራሳ፤ በክልሉ 143 ሺህ ወጣቶችን ለማሰልጠን የታቀደ ሲሆን ዘንድሮ 35 ሺህ የሚሆኑት እንደሚሰለጥኑ አስረድተዋል ።
እስካሁን በክልሉ ከ2 ሺህ 900 በላይ ተመዝግበው ሥልጠናውን እየተከታተሉ ሲሆን፤ የምዝገባና ሥልጠና ሂደቱ በተከታታይነት መቀጠሉንም አስረድተዋል።
ለዚህ ሥራ መቃናት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ በወጣቶች ማዕከላት፣ በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በኤጀንሲው ሥር ያሉ የሳይንስ ካፌዎች አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሥልጠናው ማንኛውም ዜጋ የመሳተፍ ዕድል ቢኖረውም በዋናነት ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።
ይህም እንደ አገር በሚገነባው የዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ወጣቱ ኃይል ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረውና ውጤታማ ሥራን ለመስራት እንዲችል የሚረዳ መሆኑንም አብራርተዋል።