ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሒሳብ ዘርፍ ላሰለጠናቸው ተማሪዎች እውቅና ሰጠ 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ ከቲንክ ያንግ አፍሪካና ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሒሳብ ዘርፍ (STEM) ሲያሰለጥናቸው ለቆዩ ተማሪዎች እውቅና ሰጥቷል።  

ተማሪዎቹ ከሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የተወጣጡና የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

በየእውቅና መርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ አመራሮችና የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች ተገኝተዋል።  

በኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ የማማከር ዘርፍ ኃላፊ ኤልሳ ታደለ፤ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲው ከቦይንግ ኩባንያና ከቲንክ ያንግ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመሆን በየዓመቱ እንዲህ ያለ ሥልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።


 

ይህ በአቪዬሽን ዘርፍ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ለማብቃት በሮቦቲክስ፣ በአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስና በሌሎችም ተግባራዊ ተሞክሮ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ብለዋል።

ተማሪዎቹ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ሲሆን ተማሪዎቹን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተመረጡ  ስለመሆኑም ጠቁመዋል። 

የቦይንግ ኩባንያ የአፍሪካ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሄኖክ ተፈራ በበኩላቸው፤ የቦይንግ ኩባንያ ብቁ የአቪዬሽን ሙያተኞችን ለማፍራት ከተለያዩ የዘርፉ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በዚህም ቦይንግ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ ሩዋንዳና ታንዛንያ በአቬዬሽን መስክ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ይህን ሥልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

በዘርፉ ለስድስት ሳምንታት ሥልጠናውን የወሰዱ ተማሪዎቹ በበኩላቸው፤ ለወደፊት መሆን ለሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ ሥልጠናው እንዳገዛቸውና አዳዲስ ልምዶችን እንዳካበቱ ገልጸዋል።


 

ተማሪ ሜሮን ጓዱ በአቪዬሽን ዩንቨርሲቲ ቆይቷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሁም በሮቦቲክስ የሙያ ክህሎትና በሌሎችም ዘርፍ በርካታ እውቀት ማግኘቷን ገልጻለች። 

ተማሪ ሳሙኤል  አጥናፉ በበኩሉ ወደፊት መሆን ለሚፈልገው የአውሮፕላን አብራሪነት ሙያ አሁን ላይ የወሰደው ሥልጠና በይበልጥ እንዳነሳሳው ገልጿል።

በቀጣይም እንዲህ ያሉ የክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠናዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አንስቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም