ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ የአየር መንገድ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሃና አጥናፉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰሞኑ ባጋጠመው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ፤ የመንገደኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ በረራዎች እንዲሰረዙና እንዲራዘሙ ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሃና አጥናፉ በዚሁ ጉዳይ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ በሥነ-ምግባር የተላበሰና ጥራት ያለው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ኩራት የሆነው ይህ አየር መንገድ መደበኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለደንበኞች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው በሚሰራቸው ሥራዎችም የበርካታ ስኬቶች ባለቤት የሆነ አንጋፋ ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህንን ከግምት በማስገባት ከሰሞኑ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ከትላንት በስቲያ ብቻ 42 ዓለም አቀፍ በረራዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማረፍ ባለመቻላቸው፤ ለደንበኞች ደኅንነት ሲባል አቅራቢያ ወዳሉ አየር ማረፊያዎች እንዲያርፉ መደረጉን አንስተዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ በረራዎችም በዚሁ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ መስተጓጎላቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በነበረው የአገር ውስጥ የበረራ መርኃ ግብር ወደ መቀሌ ተጉዘው የነበሩ ሁለት አውሮፕላኖች ማረፍ ሳይችሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ነው ያስታወሱት።
በዚህም ሦስተኛ በረራ ወደ መቀሌ ለማድረግ በዝግጅት ላይ የነበረው አውሮፕላንም የአየር ሁኔታው ለደኅንነት አስጊ በመሆኑ አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ሳይነሳ በረራው እንዲሰረዝ መደረጉን ገልጸዋል።
በጊዜው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች ከበረራው መሰረዝ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደኅንነት መመሪያን በሚጻረር መልኩ ያልተገባ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የአቪይሽን አሰራሮችን በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚተገበር ተቋም መሆኑን ገልጸው መሰል ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ሊታረሙና ማንኛውም መንገደኛም አሰራሮችን ሊያከብር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አየር መንገዱ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቱም ባሻገር በአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም በዓላት ሲኖሩ አየር መንገዱ ከሚሰጠው አገልግሎት በላይ የተጓዞችን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪና ግዙፍ አውሮፕላኖችን ጭምር በመመደብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም ሰሞኑን በትግራይ ክልል ለሚከበረው የአሸንዳ በዓል አየር መንገዱ ወደ መቀሌ በቀን እስከ 11 በረራዎችን እያደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገር ውስጥና በውጭ በሚሰራው ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎት ጥራትና የላቀ አፈጻጸም ተደጋጋሚ ሽልማቶች እየተበረከቱለት የሚገኝ ግዙፍ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመሆኑም ይህን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀሰውና ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆን የቻለውን አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በደንበኞች የሚነሱትን ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የቅሬታ ዴስክ በሁሉም ተርሚናሎች ውስጥ ማቋቋሙን ጠቁመው ደንበኞች ምንም አይነት ቅሬታና ችግር ካጋጠማቸው በቅሬታ ማቅረቢያ ዴስኮቹ ማመልከት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በቀጣይም አየር መንገዱ ለደንበኞች ደኅንነትና ምቾት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን በማንሳት በተለይ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግለሰቦች ደረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሥም የማጥፋት ዘመቻዎችን በማጋለጥ ከአየር መንገዱ ጋር ሊሰሩ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።