የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ዕጩ መኮንኖችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ዕጩ መኮንኖችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ለ24ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ዕጩ መኮንኖች ዛሬ በሰንዳፋ አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ በአፖስቶና ሰንዳፋ ካምፓሶች ከዋና ሳጅን ወደ ረዳት ኢንስፔክተር የማዕረግ ሽግግር ያደረጉ እንዲሁም በአንደኛ ዙር ጀማሪ የታክቲካል ወንጀል ምርመራ ያስተማራቸው የወንጀል የምርመራ የፖሊስ ኦፊሰሮች መሆናቸው ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት በፀጥታና የደህንነት ተቋማት የሪፎርም ስራ የኢትዮጵያ ፖሊስ የአደረጃጀት፣አሰራር፣ የሰው ሀብት ልማት፣ የሎጂስቲክስ፣ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ግንኙነት ላይ የነበሩ ውስንነቶች በጥናት የመለየት ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
በማሻሻያ ስራው በብዙ በርካታ መመዘኛዎች በርካታ ውጤቶች መመዘግባቸውን አመልክተዋል።
የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በማወክ፣ንጹሃንን በመግደል፣ በማገትና ሀብትና ንብረቱን በመዝረፍ ችግር በሚፈጥሩ የሽብርና የፅንፈኛ ቡድኖች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰዱ ይገኛል ብለዋል።
የአገርን ሰላምንና ደህንነት ለማረጋገጥ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር እየተወሰደ ባለው እርምጃ ፀረ ሰላም ቡድኖቹ ስጋት ወደ ማይሆኑበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ፀረ-ሰላም ቡድኖች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም በምትሰማሩበት የአገሪቷ አካባቢዎች የሕዝብና የአገርን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ዋና ተግባራችሁ ይሆናል ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ።
ተማሪዎች ምንም አይነት ልዩነት ሳይገድባቸው አገርንና ሕዝብን በእኩልነትና በታማኝነት እንዲሁም በፍፁም ቅንነትና ታማኝነት በፖሊሳዊ ስነ ምግባር እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ የትምህርት ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ሚቆሬ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሪፎርም ትኩረት ያደረገባቸው መስኮች አንዱ የሰራዊቱን የማዕረግ አሠጣጥ በስልጠና ብቻ እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህም የአመራሩን የአቅም ግንባታ ግብ ከማሳካቱም በላይ ከሪፎርሙ በፊት ለ10 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የማዕረግ አሰጣጥ ስርዓት በመመለስ የሰራዊቱን የመኮንነት ማዕረግ ወደ ተገቢው ክብሩና የከፍታ ማማው መመለስ መቻሉን አመልክተዋል።
ይህም የስራ ላይ የውድድር መንፈስ እንዲያድግ ከማስቻሉም ባሻገር ብቃት ያላቸው የፖሊስ መኮንኖችና በተሰጣቸው ማዕረግ ልክ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ የፖሊስ መኮንኖችን ማፍራት ማስቻሉን መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።