በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ የሚሳተፉ የውጭ ባለኃብቶችን ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ የሚሳተፉ የውጭ ባለኃብቶችን ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ የሚሳተፉ የውጭ ባለኃብቶችን ማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ (Ethiopian Securities Exchange - ESX) በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነት ተቋቁሟል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ማለት የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ሽያጭ፣ ግዥና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ቦታ ሲሆን ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ አማራጭ የገንዘብ ምንጭን የሚያሰፋና የተሳለጠ የግብይት ሥርዓትን የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ የሕግ ማስከበር ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ ኃብታሙ ኃይለመስቀል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ገበያው ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ መምጣቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ የመንግሥት የልማት ሥራዎች ከፋይናንስ ተቋማት ብቻ በሚገኝ ብድር ላይ የተንጠለጠለ እንዳይሆንና ከኅብረተሰቡና ከባለኃብቶች ገንዘብ መሰብሰብ እንዲችል ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኃብታሙ ገለጻ፣ በ2013 የወጣው የካፒታል ገበያ አዋጅ ላይ እንደተመላከተው የውጭ ባለኃብቶች በሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ላይ ሁለት አይነት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ዕድል ተመቻችቷል።
በአዋጁ ላይ የውጭ ባለኃብቶች በካፒታል ገበያው ላይ የአገሪቷን የኢንቨስትመንት ሕግ ባከበረ መልኩ እንደ አገልግሎት ሰጪ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዕዳ ሰነዶችንና አክሲዮኖችን በመግዛት በኢንቨስትመንቱ ላይ የመሳተፍ ዕድል ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያው አዲስ እንደመሆኗ የውጭ ባለኃብቶች በዘርፉ መሳተፋቸው የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠርና የሰው ኃይሉን ለማብቃት ወሳኝ መሆኑንም ባለሙያው ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ የውጭ ኢንቨስትመነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን የሚያሻሽልና ኢትዮጵያ ገቢራዊ ማድረግ የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቋማዊ ኢንቨስተሮች በካፒታል ገበያው ላይ እንዲሳተፉ የተፈጠረው ዕድል ሌሎች የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ በካፒታል ገበያው ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ተቋማዊ ኢንቨስተሮች ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ነው ያነሱት።
የውጭ ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በካፒታል ገበያ መሳተፍ እንዲችሉ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ የሚፈቅድ ቢሆንም በሚሸጡ የዕዳ ሰነዶችና አክሲዮኖች ላይ መሳተፍ የሚችሉባቸው ዝርዝር ጉዳዮች በቀጣይ ይወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ለአብነትም ተቋማዊ ባለኃብቶቹ ምን ያህል ሼርና ምን ያህል የዕዳ ሰነድ መግዛት እንደሚችሉ በመጪዎቹ ወራት ብሔራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በዝርዝር በሚያወጧቸው መመሪያዎች ምላሽ ያገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ ከጥቂት ወራት በኋላ ሥራውን በይፋ እንደሚጀምር አስታውቋል።