ቀጥታ፡

የአርባምንጭ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦የአርባምንጭ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ዛሬ ተቀምጧል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በላይነህ አበራ የመሰረት ድንጋዩን አስቀምጠዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ባለሀብቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የስታዲየሙ የግንባታ አማካሪ መሐንዲስ መልካም ስመኝ የስታዲየሙን ግንባታ አስመልክቶ ገለጻ አደርገዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ባስቀመጣቸው የመመዘኛ ደረጃዎች እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ 17 ሺህ ተመልካች የሚይዝ የመቀመጫ ስፍራ እንደሚገባና ስታዲየሙ የ16 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በ4 ወር እንዲሁም አጠቃላይ ግንባታው በ6 ወር እንደሚጠናቀቅ መሐንዲስ መልካም መግለጻቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘም ዛሬ ማለዳ ላይ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ሲቀላ ቀበሌ ባስገነባው አደባባይ ለስታዲየሙ ግንባታ ገቢ ማሰባሰብን አላማ ያደረገ የማስ ስፖርት መርሃ-ግብር ተካሄዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አርባምንጭ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራ ከተማ በመሆኑ በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም መገንባት አስፈላጊ ነው።

ስታዲየሙ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ የፊፋና የካፍን የግንባታ መስፈርቶች ባሟላ መልኩ እንደሚገነባም ተናግረዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ ካደረገ የተጀመረውን የስታዲየም ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚቻል መናገራቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም