በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ፔሩ አቀና - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ፔሩ አቀና
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦ በፔሩ ሊማ በሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ ወደ ፔሩ ሊማ አምርቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉና የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ እንግዳ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ለቡድኑ ሽኝት አድርገዋል።
የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ይከናወናል።
በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅታቸውን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አድርገዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም አሸኛኘት እንደተደረገለት ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ800፣1500፣ 3000 እና 5000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ10000 ሜትር እርምጃ እና በ3000 ሜትር መሰናክል በሴቶች ብቻ ትወዳደራለች።
በውድድሩ ላይ 11 ሴቶች እና 9 ወንዶች በአጠቃላይ 20 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ኢዜአ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከ134 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 720 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።