የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024/25 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከዩጋንዳው ቪላ ክለብ ጋር ያከናውናል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከሜዳው ውጪ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወቃል። ውጤቱንም ተከትሎ ንግድ ባንክ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአጠቃላይ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስና ከቡሩንዲው ቪታሎ ክለቦች አሸናፊ ጋር ይገናኛል።
ያንግ አፍሪካንስ በመጀመሪያው ጨዋታ ተጋጣሚውን ከሜዳው ውጪ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ ይታወቃል።
የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰዓት በአዛም ስፖርት ኮምሌክስ ስታዲየም ይደረጋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን የወከለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ክለቡ በ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል።