የዕዙ አባላት የህዝብና የአገርን ደህንነት ከመጠበቅ በተጓዳኝ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አሳርፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዕዙ አባላት የህዝብና የአገርን ደህንነት ከመጠበቅ በተጓዳኝ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አሳርፈዋል

ደሴ ፤ ነሐሴ 17/2016(ኢዜአ)፡-የሰሜን ምስራቅ ዕዝ የ801ኛ ኮር አባላት የህዝብና የአገርን ደህንነትና ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጓዳኝ ችግኝ በመትከል ታሪካዊ አሻራቸውን እያስቀመጡ ነው ሲሉ የኮሩ ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ተናገሩ፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ በተካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የመከላከያ ስራዊት አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በአገር መከላከያ ስራዊት ሰሜን ምስራቅ ዕዝ የ801ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ እንደገለጹት፤ ስራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየተጋ ነው፡፡
የዕዙ አባላትም የአገርን፣ የህዝብን ደህንነትና ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጓዳኝ ችግኝ በመትከል ታሪካዊ አሻራቸውን እያስቀመጡ መሆኑንም ገልፀዋል።
የዕዙ አባላት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባሻገርም በሌሎች የልማት ስራዎች በመሳተፍ ህብረተሰቡን እያገዙ ህዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
''ዛሬ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ተገኝተን አሻራችንን በማሳረፋችን ተደስተናል፣ ቀጣይም ከህዝብ ጋር ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የ02 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ መሀመድ፤ ''የአገር መከላከያ ስራዊት ሰላማችንን ከመጠበቅ በተጨማሪ በተለያዩ ልማቶች እያገዘን ነው'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ ''እኛም ከጀግናው ስራዊታችን ጎን ተሰልፈን ሰላማችንና ልማታችንን እናስቀጥላለን'' ብለዋል።
በዚህ ክረምት በመደበኛው እና ዛሬ በአንድ ጀምበር ለተተከሉ ችግኞችም ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ በተካሄደው የችግኝ ተከላ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴንን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮችና የወረዳው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።