ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ትውልድ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ታሪካዊ ተግባር ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር ፣ ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ) :- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ትውልድ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ታሪካዊ ተግባር መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

በክልሉ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደቀጠለ ይገኛል። ከቀትር በኋላ በኤረር ወረዳ ጀበርቲ ተራራ የችግኝ ተከላ ተካሄዷል። 

በመርሐ ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወየሳና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።


 

በተጨማሪም አርሶ አደሮች፣ወጣቶችና ሴቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ መሳተፋቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ የደን መራቆትን በማስቀረት አረንጓዴ ልምላሜን ማስገኘቱን አመልክተዋል።

አካባቢዎች ንፁህ አየር እንዲላበሱ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ታሪካዊ ተግባር ነውም ብለዋል።

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የሚከናወኑት የፍራፍሬ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩንና የማህበረሰቡን  የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋገጥ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው አቶ ኦርዲን የገለጹት።

በመርሐ ግብሩ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ የአርሶ አደሩ፣ ማህበረሰቡና አመራሩ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ የተተከሉት ችግኞች እንዲፀድቁ የመንከባብ ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወንም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም