የአዲስ አበባ ከተማ የሚኒባስ ታክሲ ማኅበራት ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ የሚኒባስ ታክሲ ማኅበራት ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ የሚኒባስ ታክሲ ማኅበራት በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለሚሳተፉ ሰዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሚኒባስ ታክሲ ማኅበራት ሰብሳቢ አያሌው ሥዩም ዛሬ በመዲናዋ እየተካሄደ ላለው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 1 ሺህ 200 ታክሲዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቁመዋል።
ታክሲዎቹ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ 12፡30 ባለው ጊዜ ውስጥ ሥምሪት በመውሰድ ችግኝ የሚተክሉ የከተማዋን ነዋሪዎች ወደ ተለያዩ የችግኝ መትከያ ሥፍራዎች በማጓጓዝ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን የማኅበራቱ አባላት ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ መንዲዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመገኘት አረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለነገው አገር ተረካቢ ትውልድ የለማች አገርን ለማስረከብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ይህም በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።