የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከታዳሽ ሃይል የሚመነጨውን ኢነርጂ ተደራሽነት በማስፋት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ያግዛል--ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከታዳሽ ሃይል የሚመነጨውን ኢነርጂ ተደራሽነት በማስፋት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ያግዛል--ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከታዳሽ ሃይል የሚመነጨውን ኢነርጂ ተደራሽነትን በማስፋት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ያግዛል ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ ገለጹ።
የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች ከሲዳማ ክልልና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች ጋር በመተባበር በሀዋሳ ከተማ ታቦር ተራራ ላይ ችግኝ ተክለዋል።
በተመሳሳይ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አመራሮችና ሠራተኞች በታቦር ተራራ ላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት፣ እንደ ሀገር እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከተፈጥሮ ጋር ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንድንጠቀም የሚያስገድድ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ ልማትም ከታዳሽ ሃይል የሚመነጨው ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማስፋትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝና ለኢነርጂው ዘርፍ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ውሃ፣ ንፋስና የፀሐይን ብርሃንን በመጠቀም ሃይልን ለማመንጨት የሚከናወነው ተግባር በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ታዳሽ ሃይልን ተደራሽ በማድረግ በካይ ጋዝን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በ2030 ዜጎች የታዳሽ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ አገልግሎቱ ትላልቅ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ባሉባቸው አካባቢዎችም ችግኞችን በመትከል የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል፣ ውሃ የመያዝ አቅምን ለመጨመርና ኢነርጂ የማመንጨት አቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ በአገልግሎቱ ስም የተተከሉ ችግኞችን በተገቢው በመንከባከብ ለትውልድ እንዲሻገሩ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ እድሉ በበኩላቸው 95 ከመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ሃይል ከውሃ የሚመነጭ በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የውሃ አቅምን በማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ለዜጎች ኤሌክትሪክን ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ችግኝ ከመትከል ባሻገር የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
በዛሬው ዕለትም በታቦር ተራራ አሻራቸውን ማኖራቸውን ጠቁመዋል
"በአንድ ጀምበር ተከላው የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ ለትውልድ የሚሻገር ቅርስ እንዲሆን ሃላፊነቴን እወጣለሁ" ያሉት ደግሞ በሲዳማ ክልል የአገልግሎቱ ሰራተኛ አቶ መለስ ተክላዲቅ ናቸው።
በተመሳሳይ በታቦር ተራራ በተካሄደ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር አሻራቸውን ካኖሩ ተቋማት መካከል የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው።
የፓርኩ ሥራ አስኪያጂ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ "በአንድ ጀምበር ተከላው ታቦር ተራራ ላይ አሻራችንን አሳርፈናል በዚህ ታሪክ ሰሪ ትውልድ አካል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ" ሲሉ ገልጸዋል።
የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለአካባቢው ማህበረሰብ አርአያነት ያለው ሥራ እንደሚሰራና በዚህም እንደ ሀገር ለተያዘው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ግብ መሳካት ፓርኩ የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
በፓርኩ የሚሰሩት የፌደራል ፖሊሲ አባል ኮንስታብል ድንቄ ጌታሁን በበኩላቸው በአንድ ጀምበር ተከላው በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።