ቀጥታ፡

የዛሬን ችግር ሳይሆን የነገን ፍሬ አሻግረን በማየት ለመጪው ዘመን ብሩህነት በጋራ መስራት አለብን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2016(ኢዜአ)፦የዛሬን ችግር ሳይሆን የነገን ፍሬ አሻግረን በማየት ለመጪው ዘመን ብሩህነት በጋራ መስራት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በመገኘት አሻራቸውን አኑረዋል፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ከዛሬ ባሻገር ነገን አሻግሮ በማየት በትብብር እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተመዘገበ ያለው ስኬትም ይህንን የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የዛሬን ችግር ሳይሆን የነገን ፍሬ አሻግረን በማየት ለመጪው ዘመን ብሩህነት በጋራ መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ከትናንት ታሪክ ትምህርት በመውሰድና ዛሬ ላይ በርትተን በመስራት ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ማስረከብ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።


 

በመንግስት የተጀመሩ ወደ 20 የሚጠጉ የልማት ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአቅመ ደከማ ዜጎች ቤት እድሳት፣ የተማሪ ምገባ፣ የስንዴ ልማትና መሰል ኢኒሼቲቮችን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ባለው ሂደት 39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ በዛሬው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከልናቸውን ችግኞች ሲደመሩ ወደ 40 ቢሊዮን ይደርሳሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተነሳችው በዜጎቿ የማድረግ አቅም ከፍተኛ መተማመን ስላላት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያዊያንን የመፈጸም አቅም ለዓለም ያረጋገጠ መሆኑንም አንስተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች 50 ከመቶው የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

በቀጣይም እንደ አባይ ተፋሰስ ባሉ አካባቢዎች ችግኞችን በመትከል የውሃ ጥበቃ ሥራን ልንደግፍ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለይ የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው ያነሱት፡፡

ይህም ከኢትዮጵያ ባሻገር ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም