የክልሉ ነዋሪዎች በአረንጓዴ አሻራ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በስፋት መትከል አለበት - ምክትል አፈ ጉባኤ ኤሊያስ ኡመታ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ነዋሪዎች በአረንጓዴ አሻራ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በስፋት መትከል አለበት - ምክትል አፈ ጉባኤ ኤሊያስ ኡመታ
አዳማ፤ ነሐሴ17/2016(ኢዜአ)፡- የክልሉ ነዋሪዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በስፋት መትከል አለበት ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ኤሊያስ ኡመታ ተናገሩ።
የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈጉባኤ አቶ ኤልያስ ኡመታን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የአዳማ ከተማ ከንቲባና አመራሮች የተሳተፉበት የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአዳማ ከተማ ጎሮ ወረዳ 'ጨቆኑ ጋራ' በተባለ አባባቢ ተክለዋል።
ምክትል አፈ ጉባኤው አቶ ኤልያስ ኡመታ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት አረንጓዴ አሻራ የአካባቢን ልምላሜ ከማስጠበቅ ባሻገር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችም እንዲተከሉ እድል ፈጥሯል።
በዚህም ማህበረሰቡ በተለይ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በስፋት በመትከል ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መትጋት አለበት ብለዋል።
መርሃ ግብሩ በክልሉ የተስተካከለ የአየር ሁኔታና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው መርሃ ግብሩን ይበልጥ ውጤታማ የማድረግ ድርሻ ከአመራሩ ጀምሮ የሁሉም ህብረተሰብ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ብቻ ሳይሆን የከተማው ማህበረሰብ አንድነትና ህብረቱን የሚያሳይበት ሆኗል ብለዋል።
በከተማዋ ዛሬ ለምግነትና የአካባቢውን አየር የመጠበቅ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን ገልጸው አቮካዶ፣ ማንጎና ዘይቱና እየተተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ 11 የተከላ ማዕከላት ማዘጋጀታቸውንና ህብረተሰቡ ከታዳጊ እስከ አዋቂ ሀገራዊ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
ከችግኝ ተከላው ተሳታፊዎች መካከል አቶ አለሙ በልዳና ወይዘሮ የማታወርቅ በችግኝ ተከላው መሳተፋቸው አካባቢያቸውን አረንጓዴ ከማልበሳችን ባሻገር ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በአዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ የማታወርቅ ካሳ፣ በጠዋቱ ከልጆቿቻቸው ጋር ሆነው በችግኝ ተከላው መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ሌላው የከማዋ ነዋሪ አቶ አለሙ በልዳ፣ አረንጓዴ አሻራ ተስማሚ አየር እንዲኖርና ምርታማነት እንዲያድግ የሚያግዝ መሆኑ በችግኝ ተከላው እየተሳተፉ እንደሆነ ተናግረዋል።
በቀጣይም የተተከለውን በበጋ ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ ለውጤት ማብቃት ላይም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።