በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሻራችንን በማሳረፍ የአካባቢያችንን ገፅታ እየቀየርን ነው-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሻራችንን በማሳረፍ የአካባቢያችንን ገፅታ እየቀየርን ነው-ነዋሪዎች
ሐረር፤ ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ)፡- በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሻራችንን በማሳረፍ የአካባቢያችንን ገፅታ እየቀየርን ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ችግኙን ከመትከል ባለፈ በመንከባከቡም በዛሬው የአንድነት መንፈስ እንረባረባለን ብለዋል።
በክልሉ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በተሳተፉበት በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ አረንጓዴ አሻራቸውን ሲያኖሩ ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት አረንጓዴ አሻራ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሻራችንን በማሳረፍ የአካባቢያችንን ገፅታ እየቀየርን ነው ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሰልሃዲን አህመድ "ችግኝ መትከል ህይወት እንደመዝራት ነው፤ በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።
የምንተክላቸው ችግኞች አረንጓዴዋን ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማስተላልፍ በመሆኑ በቀጣይም ተገቢውን እንክብካቤ እናደርግላቸዋለን ሲሉም ገልጸዋል።
የዕድሜ ባለጸጋው አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ በበኩላቸው "ለቀጣይ ትውልድ በማሰብና ለአገሬ ልምላሜ ባለኝ ከፍተኛ ተነሳሽነት ችግኝ ተክያለሁ" በማለት ሀገር በሚያስፈልጋት ልማት ላይ ለመሳተፍ መቼም ቢሆን እንደማይደክሙ ገልጸዋል።
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የተመለከቱት የህዝብ ተነሳሽነት ስለ አረንጓዴ አሻራ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዳላቸውና ይህም እንዳስደሰታቸው የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ ለእንክብካቤውም በዚሁ መልኩ መስራት ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ማልደው በተገኙበት የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ በርካታ ችግኞችን ሲተክሉ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ረውዳ ኡመር ናቸው።
"የምንተክላቸው ችግኞች ውበትን እየሰጡንና ጸጋን እያጎናጸፉን እንዲሁም የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስ ንጹህ አየር እንድንተነፍስ እያስቻሉን ነው"የሚሉት ወይዘሮ ረውዳ፤ ይህን ተግባር በቀጣይ ትውልድም ይጠናከራል ሲሉ ተናግረዋል።
ከአሁን በፊት የተተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ልምላሜ ወደ ነበረበት የመለሱ እና ነፋሻማ አየር ያጎናጸፉን ናቸው ያሉት መምህር አፈንዲ አልሻም፤ የአረንጓዴ ልማት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን በመገንዘብ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
"በነቂስ ወጥተን የተከልነውን ችግኝ በነቂስ ወጥተን እንንከባከባለን፤ ለቀጣይ ትውልድም አረንጓዴዋን ኢትዮጵያ እናስረክባለን" ሲሉም ተናግረዋል።
በልጅነት እድሜው የተከለው ችግኝ ትልቅ ሲሆን የሚጠቅመውና የተስተካከለ አረንጓዴ አካባቢን፣ንጹህ አየር እና ልማት እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ችግኝ መትከሉን የተናገረው ደግሞ ህፃን ቀነኒሳ ኡስማኢል ነው።