ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ የማይተካ ሚና አለው - የውጪ አገር ዜጎች

 

አደኣ ፤ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ የማይተካ ሚና እንዳለው የሩዋንዳ፣ የኬንያና የማላዊ ዜጎች ገለፁ።

ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በአደኣ ወረዳ ጎበሳዬ ቀበሌ 'ኮርፕስ አፍሪካ ኢትዮጵያ' በተሰኘ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሰማራ ድርጅት አማካኝነት የዩጋንዳ፣ የኬንያና የማላዊ ዜጎች ችግኝ ተክለዋል።

ሩዋንዳዊቷ ሊሊዓን ሩዱኩንዳ በዚሁ ወቅት እንደገለፀችው፣ ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ሊያስከትል የሚችለው ችግር ለመቀነስ ወሳኝ ነው።

በሀገሯ ሩዋንዳም አንድ ዛፍ ከተቆረጠ ሁለት ችግኞችን በመትከል በዘላቂነት የአካባቢ ስነ-ምህዳር እንዲጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሳለች።

''የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስከተለ ያለው ጉዳትን መከላከል የምንችለው ችግኝ ስንተክል ነው'' ያለችው ሊሊዓን ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በየጊዜው ችግኝ የመትከል ልምዷ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሳለች።

''በዛሬው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፌ ዕድለኛና ደስተኛ ነኝ፣ ይሄ ለኔ ታሪካዊ ቀን ነው'' ያለችው ደግሞ ኬንያዊቷ ኢዲዝ ኒያዊራ ናት።

የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እንዲሁም የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ችግኝ መትከል ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ተናግራለች።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እየተገበረች የምትገኘው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅ የማይተካ ሚና አለው ብላለች።

''ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በነቂስ ወጥቶ በችግኝ ተከላው መሳተፉ ልዩ ደስታ የሚሰጥ ነው፣ እኔና ባልደረቦቼ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ላይ መሳተፋችን ደስተኞችና ልምድ ያገኘንበት ነው'' ስትልም ተናግራለች።

ከማላዊ የመጣችው ወጣት የሚኬሜሞሪ ማኩሊን በበኩሏ ''አፍሪካን አረንጓዴ ማድረግ ከፈለግን ችግኝ መትከል አለብን፣ በዚህም የአየር ንብረት ጤንነትና አካባቢን እንጠብቃለን'' ብላለች።

በማላዊ የችግኝ ተከላ ስራው ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወን ገልጻ ኢትዮጵያ የምታከናወነውም እንደ ልምድና ተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነም ጠቅሳለች።

በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከሉ እንቅስቃሴ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም