ቀጥታ፡

ችግኞችን መትከል የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከልና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት ፋይዳው የጎላ ነው--ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ዲላ ፤ ነሐሴ 17/2016(ኢዜአ)፦ ችግኞችን መትከል በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከልና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ። 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጥላሁን ከበደ ከሌሎች የካቢኔና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በወላይታ ዞን በሁምቦ ወረዳ ካላቻ ቀበሌ ተገኝተው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በክልሉ የሚከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀግብርን ማጠናከር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከልና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥራት ለማሳካት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮም አረንጓዴ ልማቱን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር ከ3 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።


 

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ በመርሀግብሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ሀገር በቀል የደንና የፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፣ ይህም አካባቢን ለመጠበቅ፣ ለምግብ ዋስትናና ለግብርና ልማት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

በክልሉ ችግኝ መትከል የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለውን የተፈጥሮ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል ኅብረተሰቡ ችግኝ መትከሉን እንዲያጠናክረ አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሀግብር በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ለደንና ለውበት የሚሆኑ ችግኞች መካተታቸውን ጠቅሰው፣  ለተከላ በተለዩ 713 ቦታዎች ተከላው እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

553 የተከላ ሥፍራዎች ከቀጥታ የመረጃ ቋት ጋር የተገናኙ ሲሆን ኅብረተሰቡም ከሌሊቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ በመውጣት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አንደኛ ሽናሌ በበኩላቸው  በየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የችግኝ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዘመቻው ተሳታፊዎች መካከል በሁምቦ ወረዳ የጋልቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መርክነህ ባካሎ ችግኝ መትከል አካባቢን ከተፈጥሮ አደጋ ለመከላከልና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ፋይዳ እንዳለው መረዳታቸውን ገልጸዋል

በዚህም ከማለዳው ጀምሮ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ከ15 በላይ ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም በጠቅላላው 50 የሚደርሱ ችግኞችን ለመትከል አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም