የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ባህል ሆኖ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ባህል ሆኖ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2016(ኢዜአ)፦ አረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በርካታ አዎንታዊ ጥቅም ያለው በመሆኑ ባህል ሆኖ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የኃይማኖት አባቶች በአዲስ አበባ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በመገኘት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር ተሳትፈዋል።
አሻራቸውን ካኖሩት መካከል መላከምህረት ፀጋዬ ወርቁ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የአገር ገጽታ የሚለውጥ፣ ምልክትና ፀጋ ከመሆኑም በላይ ታላቅ አገር ለመገንባት አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።
ዛፎች ሰዎች ጤናማና ነፋሻማ አየር እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ፤ ወጣቶች የሚጽፉበት፣ የሚያነቡበት እንዲሁም አዛውንቶች የሚወያዩበትና የተጣላን የሚያስታርቁበት ጥላ በመሆን የሚያገለግል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሌላው የኃይማኖት አባት ሸኸ መሐመድ አወል በበኩላቸው፤ የአገር በቀል እጽዋቶች መድኃኒትም ጭምር ጠቃሚ በመሆናቸው በአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠይቀዋል።
በመሆኑም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በርካታ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ መላው ሕዝብ ያለምንም ልዩነት በዚህ በጎ ተግባር በመሳተፍ አሻራውን ሊያኖር ይገባልም ነው ያሉት።
በመርኃ-ግብሩ የተተከሉት ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ በጽናት መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
ፓስተር አብርሃም በየነ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ በመሆኑ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።