በድሬዳዋ አራቱ የገጠር ክላስተሮች የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አራቱ የገጠር ክላስተሮች የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው
ድሬዳዋ ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር አራቱ የገጠር ክላስተሮች የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
"የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ በመላው አገሪቷ እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአራቱ የድሬዳዋ የገጠር ክላስተሮችም እየተካሄደ ነው።
ከጠዋቱ ጀምሮ እየተካሄደ ባለው መርሃ ግብር በአስተዳደሩ የአሰሊሶ፣ የብየአዋሌ፣ የዋሂል እና የቀላድ የገጠር ክላስተሮች ነዋሪዎች አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ላይ ናቸው።
በቀላድ ክላስተር የለገ ዲኒ ቀበሌም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በክላስተሩ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላውን ያስጀመሩት በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት፣ ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ኡመር ዱአሌ ዛሬ ኢትዮጵያ የምታስመዘግበው አዲስ ታሪክ ባለቤት በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እና ማህበረሰብ ለመገንባት የተጀመረው ጥረት የሚሳካው በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ላይ በመረባረብ መሆኑን በማከል።
በመሆኑም በየደረጃው የሚገኘው የአስተዳደሩ ማህበረሰብ እና አመራር ዛሬ ቀኑን በሙሉ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞችን በመትከል እና በቀጣይም በመንከባከብ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፉአድ መሐሙድ በበኩላቸው ዛሬ ልዩ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቀን መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን ታሪካዊ ክስተት በተሳካ መንገድ ለመፈፀም በአስተዳደሩ አራቱ ገጠር ክላስተሮች የተቀናጀ ርብርብ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
ይህንን ደማቅ ተሳትፎ እስከ ፀሐይ መግቢያ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በማስታወስ።