ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባሻገር ሕብረ ብሔራዊ ትብብርና አንድነታችን የሚገለጽበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2016(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባሻገር የኢትዮጵያዊያን ሕብረ ብሔራዊ ትብብርና አንድነት የሚታይበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከማለዳው ጀምሮ ከልጅ እስከ አዋቂ በሁሉም አካባቢዎች አሻራቸውን እያኖሩ ነው።

በሲዳማ ክልልም ይሄው መርሃ ግብር እየተከናወነ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አሻራቸውን አኑረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ሁነት ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ በመርሃ ግብሩ በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬትም ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከልማትም ባሻገር የኢትዮጵያዊያን በሕብረ ብሔራዊ ትብብርና አንድነት የሚታይበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድነት በሕብረት ከተበባርን የአገራችንን እድገትና ብልጽግና ማሳካት እንደምንችል ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተካሄደ ይገኛል።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከማለዳ የጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እስከ ምሽት 12 ሰአት ይቀጥላል።

በመርሃ ግብሩ አዋቂዎች ከ20 በላይ፤ ታዳጊዎች ደግሞ ከ10 በላይ ችግኞችን እንደሚተክሉ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር የ600 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ሕብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም