ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ እየተከናወነ ነው

ነገሌ/ መቱ/ ጊምቢ/ነቀምቴ/አዳማ/አምቦ ፤ ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ነዋሪዎች በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተሳተፈ ነው።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ወረዳዎች ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላው እየተሳተፉ ናቸው።

በኢሉ አባቦር ዞን፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ቦረና እና አዳማ ከተማ አካባቢዎች ነዋሪዎች ችግኝ እየተከሉ ናቸው።

በአዳማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ኤሊያስ ኡመታና የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላት እንዲሁም የከተማው ከንቲባና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን አደኣ ወረዳ ጎበሳዬ ቀበሌ እየተከናወነ በሚገኘው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በተጨማሪ የወረዳው ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው እየተሳተፉ ነው።

በችግኝ ተከላው የተራቆተውን የጎበሳዬ ተራራን አረንጓዴ በማልበስ ከተራራው የሚወርደው ጎርፍ የእርሻ መሬቶችን እየጠረገ የአርሶ አደሩን ልፋት ከንቱ ያስቀረበትን ሂደት ለመግታት ነው ተብሏል።

በኢሉባቦር ዞን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሁሉም ወረዳዎች እየተካሄደ ሲሆን በተከላው አባ ገዳዎች፣ ሀዳ ሲቄዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች፣ ወጣቶች እንዲሁም ታዳጊዎች እየተሳተፉ ነው።

በአምቦ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ የከተማው ከንቲባና አመራሮችን ጨምሮ ነዋሪዎች ከማለዳ ጀምሮ እየተሳተፉ መሆኑ ተመልክቷል።

በአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም