የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2016 (ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተጀምሯል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመላው ኢትዮጵያ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
አዲስ አበባ የሚገኘው የሁኔታዎች መከታተተያና የመረጃ ማደራጃ ማዕከል የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ አስመልክቶ ያሉ መረጃዎችን እንደሚያደርስ ተናግረዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።
በዚህም በ2012 ዓ.ም 17 በመቶ የነበረው አገር አቀፍ የደን ሽፋን አሁን ላይ 23 በመቶ መድረሱን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያመለከቱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ ዓሻራችንን እናኑር ፤ አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን ሲሉ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡