በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሽኝት ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
በ17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሽኝት ተደረገለት
አዲሰ አበባ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ በሚደረገው 17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ አሸኛኘት ተደርጎለታል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ለአትሌቶቹ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ስፖርተኞቹ በድል እንዲመለሱም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በሽኝቱ ላይ የሰንደቅ አላማ ርክክብ ተደርጓል።
17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ከነሐሴ 22 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም በፓሪስ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ከ184 አገራት የተወጣጡ 4 ሺህ 400 አትሌቶች በ22 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ጾታዎች ስድስት ተወዳዳሪዎችን ታሳትፋለች።
አትሌቶቹ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ፓሪስ እንደሚያቀኑ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተያያዘም በፔሩ ሊማ ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን ሽኝት ተደርጎለታል።
በአሸኛኘቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ተገኝተዋል።
አምባሳደር መስፍንና ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ለአትሌቶቹ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ለቡድኑ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በሽኝቱ ላይ የሰንደቅ አላማ ርክክብ ስነ ስርዓት መካሄዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ800፣1500፣ 3000 እና 5000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ10000 ሜትር እርምጃ እና በ3000 ሜትር መሰናክል በሴቶች ብቻ ትወዳደራለች።
በውድድሩ ላይ 11 ሴቶች እና 9 ወንዶች በአጠቃላይ 20 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከ134 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 720 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።