ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና የሚሳተፉ ወጣቶች ምዝገባ እየተካሄደ ነው

ባህር ዳር፤  ነሐሴ  16/2016(ኢዜአ)፡-  በአገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው የኢትዮጵያውያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና ላይ በአማራ ክልል  የሚሳተፉ   ወጣቶች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን   የክልሉ ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢና የሥራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ ገለጹ። 

ለክልል ቢሮዎች  ህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች እና የ"አይ ሲቲ" ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።

በአገር ደረጃ ለሦስት ዓመት በሚሰጠው የኮደርስ ዲጅታል ቴክኖሎጅ ስልጠና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ  ወደ ተግባር የተሸጋገረ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት  ነው።

የ''አምስት ሚሊዮን ኮደርስ'' የሆነው ይሄው  መረሃ ግብር መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች በመመዝገብ ክህሎትና አለምአቀፍ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ሁሉም እንዲያበረታታ ጥሪ አቀርበዋል። 

ለዚህ ታላቅ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት  የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ትብብር ማድረጋቸውን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  አምስት ሚሊዮኖቹ ኮደርስ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን የሚሰጡ ብቻ ሳይሆኑ ለአህጉራችን የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቁም ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።

የአማራ ክልል ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢና የሥራና ስልጠና ቢሮ  ምክትል ሃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ እንዳመለከቱት፤ ለሦስት ዓመት በሚሰጠው የኮደርስ ዲጂታል ስልጠና በክልሉ  767 ሺህ 963 ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር ተግብቷል።


 

ከዚህው ውስጥ  በ2017 በጀት ዓመት "ከ191 ሺህ በላይ ወጣቶች በስልጠናው ተጠቃሚ ይሆናሉ" ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የስራ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂ የበቃ ወጣት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም በነፃ የ"ኦን ላይን "ስልጠናው መመቻቸቱን ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም የህዝብ ግንኙነት አመራር አባላት ወጣቱን በማንቃትና ስለጠቀሜታው በማስገንዘብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የኮደርስ ዲጂታል ስልጠናን ውጤታማ ለማድረግ "ስትሪንግ" እና ቴክኒካል ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።


 

ለዚህም ፍላጎቱ ያላቸውን ወጣቶች ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤  ባለፈው አንድ ወር በተደረገው ጥረትም 115 ሺህ 485 ወጣቶችን መመዝገብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

ዓለም ወደ ዲጂታል ስርዓት በፍጥነት እየመጣ በመሆኑ እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልል ከዓለም አሰራር ተነጥሎ መኖር እንደማይቻል በመገንዘበ የተመቻቸውን እድል ወጣቱ ሊጠቀምበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኮደርስ ስልጠናው ለወጣቱ ትልቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ወጣቱ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ወጣቱን የማንቃት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የክልሉ ቢሮዎች የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችና የ"አይሲቲ" ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም