በሐርላ ታሪካዊት ስፍራ- ታሪካዊ አሻራ - ኢዜአ አማርኛ
በሐርላ ታሪካዊት ስፍራ- ታሪካዊ አሻራ
በምሥራቅ ኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ አሻራ ካረፈባቸው ታሪካዊ ስፍራዎች አንዷ ናት-ሐርላ።
ሐርላ ከ10 ኛው እስከ 16 ኛው ክፍለ ዘመናት የዘለቀች የሥመ ገናና ስልጣኔ ባለቤት ናት።
የሐርላ ስልጣኔ ውጥን እና አሻራ በድሬዳዋ በስተሰሜን ምሥራቅ ጉብታ ስፍራ ላይ ትገኛለች።
በሥነ ምድር ቁፋሮ ምርምሮች የ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሳንቲሞች በሐርላ ተገኝተዋል፡፡
የሐርላ ነዋሪዎች የንግድ ግብይትና የባሕል ትስስር ከኢትዮጵያ ባለፈ ከዓረቡ ዓለም፣ ከቤዛንታይን የክርስቲያን ግዛተ አፄ፣ ከደቡብ እስያ፣ ከግብጽና በተዘዋዋሪ መንገድም ከሩቅ ምስራቅ ክፍላተ ዓለማት ጋር የተዘረጋ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ዋቢ ናቸው።
በተለያዩ ክፍለ ዘመናት የነበሩ የቻይና፣ የቤዛንታይን፣ የሕንድ፣ የስሪላንካና ሌሎች ሀገራት ስርዎ መንግስታት ሳንቲሞችና መገልገያ ቁሶች በሐርላ የአርኪኦሎጂ ቁፋሮ መገኘታቸውም ለዚህ ታሪካዊ ዕውነታ ሁነኛ አብነት ነው።
የሐርላ ከተማ መገኛ ከዛሬዋ ድሬዳዋ ራስጌ ይሁን እንጂ ግዛቷ ግን የዛሬዎቹን ሶማሊያና ጂቡቲ ያካትት እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዳንኤል ክብረት(ዲ/ን) በቅርቡ ባሳተሙት 'የትርክት ዕዳና በረከት' በተሰኘው መፅሀፋቸው አትተዋል።
"በከተማዋ ውስጥ ዋና የከተማው መንደር፤ የኢንዱስትሪ ሥፍራ፣ ሦስት መስጊዶች፣ የውኃ ጉድጓዶች፣ በሰሜን ፣ በምዕራብና በምሥራቅ የመቃብር ሥፍራዎች እና በዙሪያዋ ደግሞ የመከለያ ግንብ ነበራት" ሲሉም ጠቅሰዋል።
እንደ ድሬዳዋ ሁሉ የሐርላ ሥልጣኔ መገለጫ ኅብረ ብሔራዊነት ነበር።
"በከተማዋ አፋሮች፣ ሐረሪዎች፣ ሶማሌዎች፣ ዓረቦች፣ ፋርሶች፣ የስዋሂሊ አካባቢ ሰዎች እና ሕንዶች ይኖሩባት ነበር። በከተማዋ በቁፋሮ የተገኙት መስጊዶች አሠራራቸው ከታንዛንያና ከዘይላ ጋር የተመሳሰለ ነው" ሲሉ የሕብረ ብሔራዊነት መልኳን አብራርተዋል።
ሐርላ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች ተዳከማ ስልጣኔዋን ለሐረር ለቃለች።
በዳንኤል ክብረት (ዲ/ን) ሀታታ ሐረር ከሐርላ ስልጣኔ "የእስልምና ሥልጣኔ ማዕከል መሆንን፣ ከመካከለኛው ኢትዮጵያና ከውጭው ዓለም የነበረውን የባህል፤ የእምነትና የንግድ ግንኙነትና የከተሜነትን ባህል" አስቀጥላለች፡፡
ከድሬዳዋ በስተምሥራቅ ወጣ ብላ የምትገኘዋ የሐርላ መንደር ነፋሻማና ቀዝቃዛ አየር አላት።
የጥንት ስልጣኔ የታሪክ አሻራ ያላቸው የዛሬዋ ሐርላ መንደር ነዋሪዎች ደግሞ በታሪካዊቷ ሐርላ ለትውልድ የሚሻገር አረንጓዴ አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።
የሐርላ ቀበሌ ሊቀመንበር መሀቡ ዲኔ የሐርላ አካባቢ ተዳፋታማ ስፍራዎች ከፍተኛ መራቆት ደርሶባቸው እንደበር ያስታውሳሉ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የቀበሌውን ማህበረሰብ በማወያየትና በማሳመን በአካባቢው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተግባራዊ በመደረጉ በአካባቢው ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ያነሳሉ።
አሁንም አካባቢውን ከንክኪ ነጻ በማድረግ፣ እርከን በመስራት እና በችግኝ በመሸፈን ነጩ ተራራ ለምለሙ ተራራ የሚል ስም እንዲኖርው እየሰራን ነው ብለዋል።
በቀጣይም አካባቢው በዘላቂነት እንዲያገግም ብሎም በድሬዳዋ ከተማ ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንደሚሉት ከሐርላና አካባቢው ተራራማ ቦታዎች የሚነሳው የጎርፍ አደጋ በድሬዳዋ ህዝብ እና በመሰረተ ልማቶች ላይ መልከ ብዙ ጉዳቶችን ሲያደርስ ቆይቷል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ ሐርላና አካባቢውን በሚያካትተው የደቻቶ ወንዝ ተፋሰስ ላይ ሰፋፊ የአካባቢ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በሐርላ አካባቢ የተተከሉ ችግኞች አካባቢውን እየለወጡት መሆኑን ገልጸዋል።
የሐርላ ተዳፋታማ ስፍራ መራቆቱን ተከትሎ አካባቢው ነጭ ተራራ የሚል ስያሜ እንደነበረው አስታውሰው፤ አሁን ግን ህብረተሰቡን በማስተባበር በተሰሩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ገፅታውን በመቀየር የተራቆተው ቦታ እያገገመ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ችግኞች ለመትከል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል።
የታሪካዊቷ ሐርላ መንደር አካባቢም በነገው ዕለት በስፋት ችግኝ ከሚተከልባቸው የተለዩ ስፍራዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
ሐርላ ከድሬዳዋ አቅራቢያ የተሻለ የአየር ንብረት ያላት በመሆኗ ወደፊት አካባቢውን በማልማት ለኢኮቱሪዝም አገልግሎት መጠቀም እንደሚቻል ነው ያነሱት።
በሞቃታማዋና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነችው ድሬዳዋ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ከችግኝ መትከል ያለፈ ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ በነገው የችግኝ ተከላ ንቅናቄ በነቂስ ወጥቶ አሻራውን እንዲያሳርፈ ጥሪ አቅርበዋል።
ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አይተኬ ሚና ያላቸው የችግኝ ዝርያዎች እንደሆኑ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተማ አስተዳደሩ ለጎረቤት ሀገር ጅቡቲ በየዓመቱ ችግኞችን እንደሚያበረክት አስታውሰው፤ ዘንድሮም 100 ሺህ ችግኞች ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህም የጋራ ችግር የሆነውን የአየር ንብረት ተጽእኖ ለመቋቋም ካለው ፋይዳ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጎለበት ያግዛል ብለዋል።