የአሸንዳ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የድርሻችንን እንወጣለን-- የበዓሉ ታዳሚዎች

መቀሌ ፤ነሐሴ ፤16 /2016 (ኢዜአ)፦ የአሸንዳ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በመቀሌ ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የታደሙ ልጃገረዶች እና እናቶች ተናገሩ።

ልጃገረዶች እና እናቶች ዛሬ በመቀሌ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር በዓሉን በድምቀት አክብረዋል። 

በበዓሉ ከተገኙት የመቀሌ ከተማ ልጃገረዶች መካከል የ20 ዓመት ወጣት ሃረርታ ገብረጻድቅ አንዷ ናት። 

በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በደመቀ ሁኔታ በሚከበረው በዓል ላይ እንደምትገኝ ገልጻ፤ ዛሬም የበዓሉን ባህላዊ ይዘትና ታሪክ ጠብቃ ማክበሯን ተናግራለች። 

"የአሸንዳ በዓል ሲከበር ከአለባበስ ጀምሮ እስከ ፀጉር አሰራር ባህሉን የጠበቀ ሊሆን ይገባል" የምትለው ወጣት ሃረርታ፣ ይህም ከወላጆች ጀምሮ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለጸችው።

የእናትዋን ባህላዊ ልብስ በመዋስ በዓሉን ለማክበር መምጣቷን የተናገረችው ወጣት እሌኒ በርሀ በበኩሏ፣ ባህላዊ ጌጣጌጦችን አስቀድማ በመግዛት ለበዓሉ ድምቀት የበኩልዋን ድርሻ መጫወትዋን ትናገራለች። 

አሸንዳ በየዓመቱ በደመቀ መልኩ እንዲከበርና ለትውልድ እንዲተላለፍ ልጃገረዶች ከአለባበስ ጀምሮ የሚያደርጓቸው ጌጣ ጌጦችና የሚዘፍኑዋቸው ዘፈኖች በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል ያለችው ደግሞ ወጣት ሙሉ ኪሮስ ናት። 

የመቀሌ ሆስፒታል ሠራተኛ ወይዘሮ አለምነሽ በርሀ በበኩላቸው፣ አሸንዳ ባህሉን ተጠብቆ ወደ ተተኪ ልጃገረዶች እንዲተላለፍ ምሳሌ ለመሆን በማሰባቸው በበዓሉ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። 

"እኛ እናቶቻቸው ካላስተማርናቸው ልጃገረዶች ባህሉን በሚገባ ሊወርሱ አይችሉም" የሚሉት ወይዘሮ አለምነሽ፤ በበዓሉ ወቅት የሚለበሰው ልብስ ጨምሮ ለማጋጌጫ የምንጠቀመውንና የፀጉር አሰራር ምን እንደሚመስል ለማሳየት በቡድን ሆነው በዓሉን እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የነርስ ባለሙያ ሲስተር መረስዒት ተስፋይ በበኩላቸው፤ ባህል እንደ ዱላ ቅብብል ስለሆነ የአሸንዳ በዓል ባህላዊ ይዘት ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር የድርሻቸውን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

"ከእናቶቻችን የወረስነው ባህል ሳይበረዝ ተጠብቆ ወደ ትውልድ እንዲሻገር ከልጆቻችን ጋር በጋራ እያከበርን እንገኛለን" ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃን ብርሃኑ ናቸው። 

በበዓሉ ተሳታፊ እናቶች እንዳሉት የአሸንዳ በዓል በየዓመቱ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር በዋነኛነት ወላጆች ሃላፊነት አለባቸው።

በዚህም ስለበዓሉ ተሳታፊዎች አለባበስ፣ የሹሩባ አሰራር እንዲሁም ስለዘፈኖች እና ማጋጌጫዎች ለልጆች በማስተማር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም