ቀጥታ፡

በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል-የኢታንግ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች

ጋምቤላ/ገረሴ   ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፡- የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

በተመሳሳይ በጋሞ ዞን የገረሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ለነገው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ነገ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓሻራችንን እናኑር በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት ማስተላለፋቸው የታወሳል።

በዚህም አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኞች በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ማለታቸው ይታወቃል።

በዚህም  የኢታንግ ልዩ ወረዳ  የድርሻውን ለመወጣት  ዝግጅት መጠናቀቁን የልዩ ወረዳው አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የአካባቢው ነዋሪዎቹም በመረሃ ግብሩ ለመሳተፍ   ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል

ከልዩ ወረዳው የኢባጎ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኡጁሉ የቻለና ወይዘሮ አሞድ ኡቦንግ ፤ ለነገው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ላይ ለመሳተፍ መሰናዳታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብር በመሳተፍ አሻራቸውን ለማኖር ዕለቱን  በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተከላውን ለማከናወን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮና ችግኝ ማጓጓዝ ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ እንደቆዩም አመልክተዋል። 

የልዩ ወረዳው አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ኡዋር ኡቻን እንደተናገሩት ፤ ነገ  በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል።

በልዩ ወረዳው  በተመረጡ ስምንት ቦታዎች ሕዝቡን በማስተባበር ችግኞች እንደሚተከሉም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በጋሞ ዞን የገረሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል  አቶ መንግስቱ ማርማጫ፤  ለነገ  የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሸራ ችግኝ ተከላ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

 በዚህ ታሪካዊ ቀን አሻራቸውን ለማስቀመጥ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ወይዘሮ እመቤት ቡንፔ በበኩላቸው፤ አካባቢያችን ተራራማ በመሆኑ ለመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንዳይጋለጡ  የአረንጓዴ አሻራ ልማት አስተዋጽኦው ጉልህ ነው ብለዋል።

ለነገው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ  ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የገረሴ ዙሪያ ወረዳ ደንና አከባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙሴ ሙዳ በበኩላቸው፤ ለአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር በ5 ሺህ 932 ሄክታር በሚሸፍን ቦታ ላይ ችግኝ እንደሚተከል አስታውቀዋል።

ለዚህም ችግኝና የመትከያ ጉድጓዶች ተቆፍረው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም