በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን እንተክላለን

በቃለአብ ጳውሎስ (ኢዜአ) 

ኢትዮጵያውያን በወርሃ ነሐሴ አጋማሽ በዕለተ ዓርብ በነቂስ ወጥተው በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። በዚህም ኢትዮጵያና ልጆቿ የዓለም ክብረ ወሰን በጃጀቸው ለማድረግ ነገን በናፍቆት እየጠበቁ ነው።

ዓርብ ከነሀሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ አሻራችንን ለቀጣይ ትውልድ የምናኖርበት  ዕለት ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በመላ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች በመላ ኢትዮጵያ በመጀመሪያዉ ምዕራፍ ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የደንን የፍራፍፍሬና ለሌሎች ግልጋሎት የሚውሉ የችግኞች ተተክለዋል።  ለተተከሉት ችግኞች በዘርፉ ሙያተኞች ጭምር በተደረገው ከትትል ከመካከላቸውም 90 በመቶ ያዕሉ መፅደቃቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

የተፈጥሮ ሃብትና የሕይወታዊ ሃብት ጥበቃ ሥራ ሲጠናከርና ተከታታይነት ባለው መንገድ ሲሰራ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ነጻ የሆነና መልካምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ አካባቢያዊ የአየር ንብረት እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እድል ይሰጣል፡፡ የልምላሜ ስነ ልቦናዊ፤ ሠላም፤ ደስታ፤ ፍቅርና ተስፋዎችም ይሰጣሉ፡፡ 

በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመላ አገሪቱ በተተከሉ ችግኞች ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩና የአፈር መሸርሸር አጋጥሟቸው የነበሩ አከባቢዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ገፅታቸው እየተመለሱና መሬቱም እያገገመ መሆኑን የግብርና ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ሥራችን በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶችን እያሳየን ይገኛል፡፡ 

የአረንጓዴ አሻራ ልማት ቀጣይነት ባለው መንገድ በተከታታይ መካሄድ ከጀመረ ጀምሮ ቀደም ሲል ተደጋጋሚ ለድርቅ ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎች ዝናብ ማግኘት ጀምረዋል፤ በደን በተሸፈኑ አከባቢዎች የጎርፍ አደጋን መቀነስ ተችሏል፤ የደረቁ ምንጮችና ሀይቆች እንደገና ቀድሞ ወደ ነበሩበት መመለስ ችለዋል፤ ለበጋና የመኸር እርሻ ተስማሚ የሆነ ዝናብ ማግኘት ተችሏል፡፡

ከሥራ እድል ፈጠራነት አንጻር ለእንስሳት መኖነት፣ ለንብ ማነብ፣ ለካርቦን ሽያጭ በሚውሉ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ፈጠሯል።ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ችግኞችን አዘጋጅታ በመስጠት ምር”የአረነጓዴው አሻራ መርሃ ግብር አካል እንዲሆኑና  መልካም ጉርብትናቸው ተጠናክሮ እነዲቀጥል  በማድረግ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ገበር ለዲፕሎማሲ ግንኝነት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ132 ሺህ 144 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች ለመትከል በመላ ኢትዮጵያ የቅድመ-ተከላ ዝግጅቶች ተጠናቀው በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በመርሃ ግብሩ  ከሚተከሉት ችግኞች መካከል ተከላ 25 በመቶ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰሶች የሚተከል ይሆናል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅትና ተከላ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል እየፈጠ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ 

በዘንድሮው የችግኝ ተከላ በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች የስነ-አካላዊ ስራ በመስራት በስነ-ህይወታዊ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ገቢ የሚየስገኙ አትክልትና ፍራፍሬ፤ ጥምር ደን፤ ለከተሜነት ዉበት የሚዉሉ እና ለደን የሚዉሉ ናቸዉ፡፡ ለሁለተኛው አረንጓዴ አሻራ ሁለተኛ ዓመት የአረንጓድ አሻራ ስኬት የሁላችንም ተሳትፎና ዝግጁነት ከወዲሁ ይጠበቃል፡፡

እ.አ.አ. ከ1970 ጀምሮ እየተከበረ ያለው የዓለም 'የመሬት ቀን'ም ጤናማና ዘላቂ ከባቢ መገንባት፣ ለነገ ትውልድ የተሻለ ዓለም ማውረስን ለማበረታታት ያለመ ነው። የዓለም አርሶ አደሮች የአዝዕርት ዝርያዎችን ጠብቀውና አላምደው ዘመናትን ተሻግረዋል። ዳሩ በኢንዱስትሪና እርሻ መስፋፋት ሳቢያ 75 በመቶው የዕጽዋት ዝርያ መጥፋቱን የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ ያሳያል። "ሚሊኒየም ኢኮሲስተም አሰስመንት" የተሰኘ ድረ-ገፅ እንዳስነበበው ደግሞ ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ የዕፅዋት ዝርያዎች የሕልውና አደጋ ተደቅኖባቸዋል።

በዚህም ባለድርሻ አካላት በየፊናቸው ችግኝ ተከላን በማስፋፋት የተፈጥሮ ሚዛንን ለመመለስ እጎተጎቱ ነው። መንግሥታትም እንደየነባራዊ ሁኔታቸው የራሳቸው ተሞክሮ አላቸው። የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት፣ የምድር መጎሳቆልና የዕጽዋት መመናመን ጉዳይ ያሳሰባቸው ግለሰቦች፣ ማህበራት፣መንግሥታዊና  መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በየፊናቸው አመርቂ ተግባራት አከናውነዋል፤ እያከናወኑም ይገኛሉ። ኢትዮጵያም በተፈጥሮ ኃብት፣   በደን ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወንና ልምዷን ለማካፈል በዓለም ላይ ተጠቃሽ ተሞክሮ ሰንቃ ሀገር ሆናለች።

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ምድራዊ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ኃብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በሂደት ግን በብዝኃ-ሕይወት መመናመን ምክንያት ጥቅል የደን ሽፋን ወደ 3 በመቶ መውረዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደረጉ ጥናቶች ደግሞ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከ17 በመቶ  በላይ ዕድገት መሳየቱ  ይነገራል።

የኢትዮጵያን የደን ልማት ጅማሮ መቼት በእርግጠኝነት ለመናገር አዳጋች እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዘትና ቅርጹ ይለያይ እንጂ ነባር የችግኝ ተከላ ባህልና ልምድ እንዳለው ያወሳሉ። ያም ሆኖ በሺህ ዘመናት ባለታሪኳ ኢትዮጵያ ደን ድንናን መንግሥታዊ ቁርጠኝነት ወስደው የሰሩ መሪዎችም ነበሯት። ለአብነትም በመካከለኛው እና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ተሞክሮዎችን ማውሳት ይቻላል።

ከመካከለኛው ዘመን ታሪክ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መካከል አፄ ዳዊት ከ1375- 1404 በነበሩ የግዛት ዘመናቸው ደን ጭፍጨፋና የእንስሳትን አደን ለመከላከል በአገሪቱ ሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች አቋቁመው እንደነበር ዜና መዋዕላቸው ይናገራል። ልጃቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብም በጅባት፣ በወፍ ዋሻ፣ የወጨጫን፣ መናገሻና የየረር ጋራዎችን የደን ክምችት ጥበቃ አጠናክረዋል፤ ‘የንጉሥ የደን ክልል’ አሰኝተው ኢትዮጵያን የደን ካባ ለማልበስ ጥረዋል። 
ችግኞችን አፍልቶ የመትከል ሥራዎች ደግሞ በአፄ ልብነ-ድንግል ዘመነ-መንግሥት ስለመጀመራቸው ይወሳል። ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በሚገኘው የሱባ ደንም ንጉሠ-ነገሥቱ ከወፍ ዋሻ የዛፍ የሱባ/መናገሻ/ ደን ውስጥ ዛፎችን ስለመትከላቸው ይነገራል። በእርግጥ በመካከለኛው ዘመን ደን የመንከባከብና ዛፍ የመትከል ጅማሮ በዘመነ-መሳፍንት እንደተዳከመ ይነገራል።

ሌላው በደን ድነና ታሪካቸው የሚነሳው አፄ ምኒልክ ናቸው። የአፄ ዘርዓ ያዕቆብን ‘የንጉሥ ደን ጥብቅ ሥፍራ’ ፅንሰ-ሃሳብን አጠናክረዋል። በዘመናቸው ያጋጠማቸውን ፈተናም ለደን ድንና ተጨማሪ ኃይል የገፋፋቸው ይመስላል። አፄ ምኒልክ የደን የሕግ ማዕቀፍ አውጥተዋል፤ አማካሪም ቀጥረዋል። ደን ሁሉ የመንግሥት ንብረት እንዲሆንም ደንግገዋል። ፈጥኖ-አደግ የዛፍ ዝርያዎችን ከውጭ አስመጥተዋል። ዛሬ አገሪቷን የተቆጣጠረው አውስትራሊያዊው ባሕር ዛፍ (ኢካሊፕተስ) የትመጣነቱ ዳግማዊ ምኒልክ መሆኑ እሙን ነው። 

አፄ ምኒልክ በመንግሥት ከሚለማው ደን በተጨማሪ ተራው ዜጋ በባለቤትነት በደን ልማት እንዲሳተፍም አዋጅ አውጥተው እንደነበር የመዕዋለ ዜና ዘጋቢያቸው ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደ አረጋይ ጽፈዋል። አዋጁም ዛፍ የተከለ የመሬት ግብሩን ምሬዋለሁ የሚል ነበር። ለደን ጨፍጫፊዎችም ንብረታቸውን እንዲወረስና ብርቱ ቅጣት እንዲቀጡ ሕግ አርቅቀው እንደነበር ይወሳል። አፄ ምኒልክ ራሳቸው ከተከሏቸው የዛፍ ችግኞች መካከል በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን እና በደቡብ ወሎ ወረኢሉ ከተማ የሚገኙት ተጠቃሽ ናቸው።
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥትም ዛፍ መትከል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደነበር ይነገራል። በደርግ ዘመን የተከሰተው ድርቅና ረሀብ ደግሞ በኢትዮጵያ ለሌላ ተጨማሪ የችግኝ ተከላ ዘመቻ መንስዔ ሆኗል። በደርግ ሥርዓተ-መንግሥት ችግኝ ተከላ እንደ አፄ ምኒልክ ለችግኝ ተካዩ ማበረታቻ የሚያሰጥ ተግባር ሆኖ እንደነበር ይነገራል። በአካባቢ ጥበቃ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች ተቀርጸው ገቢራዊ ተደርገዋል። በወቅቱ የተደረገው የተራቆቱ አካባቢዎችን በተለይም ተራሮችን ዛፍ የመትከል ዘመቻ ፍሬ አፍርቷል። ዛሬ በበርካታ የአገሪቷ አካባቢዎች የደን ጸጉር የለበሱ ተራሮች ሕያው ምስክር ሆነዋል። የደርግ ዘመን አረንጓዴ አሻራዎች ዛሬ የተራሮች አረንጓዴ ዕንቁ ሆነዋል። በደርግ ዘመነ-መንግሥትም የአካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከደን መመናመንና ከተፈጥሮ ኃብት መራቆት ጋር ተያይዞ አፍሪካና ኢትዮጵያ ያጋጠማቸውን ቀውሶችና ያለባቸውን ተግዳሮቶች ለምዕራቡ ዓለም አስረድተዋል፤ ተሟግተዋልም። አቶ መለስ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እስከማለት ድረስ የዘለቁበትና ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቁት ፓኬጅም የሚጠቀስ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ቢኖሩም ዳሩ በዘመነ-ኢሕአዴግ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የደን ውድመት የደረሰበት ወቅት እንደነበር ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ኃብት መንከባከብን ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል። ከ2011 ዓ.ም የክረምት ወቅት ጀምሮ በየዓመቱ ‘አረንጓዴ አሻራ’ ገቢራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። በመላ አገሪቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እያሳተፈ መርሃ-ግብሩ እንደቀጠለ ነው። ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ያደረገ ተግባር ነው። አሁን ላይ ደግሞ የችግኝ መትከል ባህል ከመንግሥት ቅስቀሳና ከግለሰቦች ጥረት ባለፈ ሀገራዊ ቅርፅ የያዘ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትልቁ ማሳያ ነው።
በመሪዎች ደረጃ ይህን አነሳን እንጂ በየዘመኑ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማትም ተፈጥረዋል፡፡ ዛፍ እንደ ቅርስ፣ እንደ ሐውልት ታሪክ ማስተላለፊያ ነውና በየዘመኑ ትጉ ሰዎች ለትውልድ ቅርስ ትተው አልፈዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ ፋይዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2012 የዓለም አካባቢ ቀን በተከበረበት ዕለት “ብዝኃ- ሕይወትን መጠበቅና መንከባከብ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና መሆኑን አይተናል” በማለት የአካባቢ ደኅንነት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አረጋግጠዋል። እንደ ሌላው ክፍላተ-ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት ችግር ተጋርጦባታል፤ ለጎርፍ አደጋ፣ ለአፈር መሸርሸር፣ ለደን መጥፋትና ለብዝኃ-ሕይወት ኪሳራ ዳርገዋታልም ብለዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታዎችን የማመቻቸት አካል መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ ግብ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞን ለመትከል ራዕይ እንድትሰንቅ እንዳስገደዳትም ተናግረው ነበር። ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ደግሞ ‘አረንጓዴ አሻራ’ ተሰኝቷል።የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ገብር ክዋኔም በአራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ተወጥኖ፤ አፈጻጸሙ ከዕቅድ በላይ ሆኖ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መተከላቸውን መረጃዎች  ያስረዳሉ። የአራት ዓመታት የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተጠናቆ ሁለተኛው ምዕራፍ  በቀዳሚው ዓመት መጀመሩ ይፋ ሆፐኖ  ዘንድሮ ሁለት ብሏል። 

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ አጀማመር

የመጀመሪያው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በ2011 ዓ.ም  በይፋ ሲጀመር አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቶ በድምሩ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተቀምጦ ነበር። መላ ከ20 ሚሊዮን የሚልቁ ኢትዮጵያውያን የመሪያቸውን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐበይን ፈለግ ተከትለው ለመርሃ ገብሮቹ ተግተው በመረባረባቸው ከዕቅድ የ5 ቢሊዮን ብልጫ ያለው ችግኝ በመትከል  ከተቀመጠው ግብ በላይ ተሳክቷል።

በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2012 ዓ.ም 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል። በተለይ የፍራፍሬ ተክሎች ትኩረት ተሰጥቶት ነበር።
በ2013 ዓ.ም የተካሄደው ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መሪ ሀሳብ ተተግብሮ ሯል። ይህም ዙር ችግኞችን ለጎረቤት አገራት በመስጠት ኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ አርዓያ እንድትሆን በማስቻል ድንበር ዘለል በመሆኑ ለየት ያለ ባህሪ የነበረው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ችግኞችን በመለገስ የልማት አቅጣጫዋ ከጎረቤቶቿ ጋር አብሮ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ መሆኑን በተግባር አስመስክራለች።

ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም "አሻራችን ለትውልዳችን" በሚል መሪ ሀሳብ በይፋ የተጀመረው አራተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ የችግኝ  ተከላ መርሃ-ግብር  6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ  ከዕቅድ በላይ መሳካቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በቅርቡ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጋዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በችግኝ ተከላው  በየዓመቱ በአማካይ 20 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳትፏል። ከተተከሉት ችግኞች መካከል 52 በመቶ የጥምር ደን እርሻ፣ የፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ ናቸው። ሀገር በቀል ዝርያዎች ከፍተኛ ትኩረት ማግኘታቸውን አንሰተዋል። የፅድቀት መጠናቸው ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ ተሻግሯል።

የችግኝ ጣቢያዎች ብዛት፣ ደረጃ፣ ጥራትና አቅም አድጓል። ከመጀመሪያው ምዕራፍ ትሩፋቶች መካከል አረንጓዴ የአኗኗር ዘይቤ መፈጠሩ፣ የደን ጭፍጨፋ ምጣኔ በግማሽ እንዲቀንስ ማስቻሉ፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ለብዙዎች የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የተራቆቱ አካባቢዎችና ተፋሰሶች እንዲያገግሙ አስችሏል። ባገገሙ ተፋሰሶችም በርካታ አርሶና አርብቶ አደሮች በንብ ማነብና በእንስሳት መኖ ልማት በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጧል። ለአብነትም በመርሃ ገበሮቹ የተተከሉ የአቮካዶ ምርት ለውጭ ገበያ በመቅርቡ  ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አቮካዶ አምራች ለመሆን መብቃቷንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ሁለተኛው ዙር የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር መሪ ሀሳብ 'ነገን ዛሬ እንትከል' የሚል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በአፋር ክልል የሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር ማስጀመራቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት እንዳሉት በቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው ሁለተኛው ምዕራፍ 25 ቢሊዮን ችግኞች ይተከላሉ። እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም በሚዘልቀው የዘንድሮው መርሃ- ግብርም 60 በመቶ የጥምር ደን እርሻ ችግኞች፣ 35 በመቶ ደግሞ የደን ችግኞች ሲሆኑ 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ችግኞች ናቸው። ለልጆቻችን ዕዳ ሳይሆን ልማትን ማሸጋገር እንደሚገባም ተናግረዋል። በዚህም ዛሬ ያለው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የማሸጋገር ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበትም በአጽንዖት አስገንዝበዋል።

ነገን ዛሬ የመትከል ሥራችንን በአስተማማኝ ሁኔታ እያረጋገጥን በውጤታማነት ለመቀጠል እየሰራን ነው' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጥራት ጉዳይ የአረንጓዴ አሻራ ትኩረት እንደሚሆን ገልጸዋል። በተለይም ለፍራፍሬ እና ሀገር በቀል ዛፎች ቀዳሚ ትኩረት መሰጠቱን አስታውሰዋል። እንደየመልክዓ-ምድሩ ዓይነት ተስማሚና በአጭር ጊዜ ለምግብነት የሚደርሱ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የራስ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያለመ ነው። ውበት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ገቢ አበርክቶ ያላቸው ችግኞች ላይ ይተኩሯል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሮች ዓመታት በአጠቃላይ 50 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን ገፅታ መለወጥ፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የአቮካዶ አምራች ሀገር ማድረግ መሻት ያላት ሲሆን፤ ለስኬታማነቱም ጥራት ያለው ፖሊሲ ገቢራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል። ያለ ልዩነት ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ስኬት መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)  እንዳሉት፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ገበር  7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል። የሚተከሉ ችግኞችን በቴክኖሎጂ መከታተል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ክትትል ይደረጋል። በሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የምግብ ዋስትናን እና የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ፣ የካርቦን ፋይናንስ ገቢን በሚያሳድግና የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ስኬትን በሚያግዝ መልኩ ይተገበራል።

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የአገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችው አየር ንብረትና መልክዓ-ምድር ለዚህ የሚጋብዝ ነው። ደን ልማት ዘላቂ ሥራ መሆን አለበት። ባለቤትነት እንዲጨምርም በወል መሬት ብቻ ሳይሆን በግል ይዞታም አረንጓዴ አሻራ መተግበር አለበት። የደን ልማት አካል የሆነው አረንጓዴ አሻራ አገራዊ ፋይዳው ሁለንተናዊ ነው። የአረንጓዴ አሻራ ልማት አገራዊ ፋይዳው ባለፈ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ በረከቶችን ተሸክሟል። የደን ልማት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው የሚባለው ለዚህ ነው።የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ውጥን በአገሩ ጉዳይ አንድ የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገ በነቂስ ወጥቶ  እንደሚያሳካውና ኢትዮጵያው የዘርፉን የክብረ  ወሰን ባለቤት እንደምትሆን ሁሉም እርግጠኛ ሆኖ ነገን በጉጉት እየጠበቀ ነው። የነገ ሰው ይበለን!
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም