ቀጥታ፡

በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ  ተዘጋጅተናል-የክልል ነዋሪዎች

ክልል ፤ ነሐሴ16/2016(ኢዜአ)፡- በነገው ዕለት በመላው አገሪቱ ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አረንጓዴ ዐሻራቸውን ለማሳረፍ መዘጋጀታቸው የተለያዩ ክልሎች ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሲዳማ ክልሎች ነዋሪዎችን አነጋግሯል። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዋካ ከተማ ነዋሪው አቶ ደስታ ደምሴ ለዝናብና ብርድ ሳይበገሩ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተከላ ቦታ በመገኘት ዐሻራቸውን ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ እስክንድር ተፈራ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለቸው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ዘመን ተሻጋሪና ለትውልድ የሚተርፍ ተግባር በመሆኑ ድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቼያለሁ ብለዋል። 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ የጠዛ ገርባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መስፍን ሄሴቦ በበኩላቸው ችግኝ መትከል ለተተኪው ትውልድ የለማች ሀገር ለማስተላለፍ ስለሚያስችል ነገ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ እሳተፋለሁ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ችግኝ የምግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥም ጭምር በጎ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል" ያሉት ደግሞ የዱራሜ ከተማ ነዋሪ ወጣት ድንቅነህ ዓለሙ ነው።

የችግኝ ተከላ በምግብ ራስን በመቻል ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ስለሚያግዝ  በነገው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር  እንደሚሳተፉ ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሐረርጌ፣ ምስራቅ ቦረና፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎችም ነገ ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መዘጋጀታቸውን ነው ለኢዜአ የገለጹት።

የጭሮ ወረዳ አስተዳደር መንግስት ሠራተኛ አቶ በድሪ መሀመድ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ አሻራ የሚያኖሩበት አጋጣሚ በመሆኑ ከጠዋት ጀምሮ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል።

''ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ እየተሳተፍኩ ነው'' ያሉት አቶ በድሪ  በየአመቱ የህዝቡ ተሳትፎ እያደገ መምጣት ይበልጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

ከችግኝ ተከላ እስከ እንክብካቤ በትኩረት በመሳተፍ እንደ አንድ ዜጋ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መሐመድ ኢድሪስ ናቸው፡፡ 

ችግኝ መትከል ብቻውን በቂ ባለመሆኑ እንደ ተከላው ሁሉ ለእንክብካቤውም ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ ቦረና ዞን የሊበን ወረዳ ነዋሪ አቶ አሬሮ ጅሎ፣ የአካባቢ መራቆትን በመከላከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ችግኝ መትከል ብቻውን በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

በአፈርና ውሀ ጥበቃ፣ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ስራ በመሳተፍ ከአምስት ዓመታት የዘለለ ልምድና ተሞክሮ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

''ነገ የምንተክለው ችግኝ ችግኝ ለውጤት እስኪበቃ የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ የሁላችንም ድርሻና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል'' ብለዋል፡፡

አቶ ለገሰ ኑራ፣ በአከባቢያቸው ባለፉት አመታት በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉት ችግኝ ቁመና ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደገፋ ኦልአኒ በበኩላቸው ዘንድሮም አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ መንጎና የመሳሰሉትን መትከላቸውን ተናግረው ለነገው መርሃ ግብርም ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

''በየዓመቱ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚተከሉ ችግኞን የመንከባከብ እና እንዲፀድቁ ማድረግ ባህላችን ሊሆን ይገባል'' ያሉት ደግሞ የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ገምታ ዋቅቡልቾ ናቸው፡፡

በነገው እለትም ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ችግርኝ ለመትከል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አቮካዶ፣ ዘይቱን፣ ቴምርና ለደን አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች ትኩረት የተሰጣቸው መሆነን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ናቸው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን ነዋሪ ወጣት ክብረት ሳሙኤል  እና አቶ ታደሰ ከተማ  ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

"ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር በመሆን ከኅብረተሰቡና ጋር በጋራና በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ በጓሮአቸው ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅቼያለሁ ሲሉም አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

በወላይታ ዞን የሶዶ ከተማ ነዋሪው አቶ ተፈራ ዳርጮ በበኩላቸው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ላይ ለመሳተፍ ቀኑን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

"ችግኝ መትከል ህይወትን ማስቀጠል ነው" ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ጀምሮ በየዓመቱ የሚጠበቅባቸውን ሲወጡ  መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

በተያያዘ በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ሽመልስ ነጋ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ታቦር ተራራ ላይ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም