በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል- የሀረሪ ክልል ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል- የሀረሪ ክልል ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦በአንድ ጀምበር የ600 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ላይ ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የሀረሪ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 17 በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር በማለት ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
የሀረሪ ክልል ነዋሪዎችም ጥሪውን በመቀበል በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ላይ ለመሳተፍ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ የአንድነት ገመድ ነው ብለዋል።
በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካትና የታሪክ ተጋሪ ለመሆን ነዋሪው በራሱ ፍላጎት እንደከዚህ ቀደሙ በነቂስ በመውጣት ለመትከል ቀኑን በጉጉት እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እቅዱን ለማሳካትና በአረንጓዴ አሻራው አዲስ ታሪክ ለመፃፍ በክልላችን በተዘጋጁ የመትከያ ስፍራዎች ላይ ከንጋት እስከ ምሽት እንተክላለንም ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት አገር የማልማትና ማሳደግ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው ባለፋት አመታት የተተከሉ ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ህዝቡ ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሳይል ሁሉም ዜጋ በነቂስ በመውጣት በችግኝ ተከላው ላይ መሳተፍና ሀገራዊ ሀላፊነቱን መወጣት ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።