በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር አሻራችንን በማኖር ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል--ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር አሻራችንን በማኖር ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል--ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች
ዲላ ፤ነሐሴ ፤16 /2016 (ኢዜአ)፦ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሻራችንን በማኖር ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።
የፓርቲ ተወካዮች በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ዛሬ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት አሰፋ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀግብር ለመጪው ትውልድ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር መሰረት የሚጥል ነው።
"በችግኝ ተከላ መሳተፍ ነገን ተስፋ ከሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቅ ነው" ያሉት ሰብሳቢው፣ በክልሉ እየተንቀሳቀስን ያለን የፖሊቲካ ፓርቲዎች አባሎቻችንን በማስተባበር በነገው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር በመሳተፍ አሻራችንን ማኖር አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ታምራት፣ ችግኝ በመትከል ለአገር ልማት የምናሳየውን አብሮነት ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ማዋል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን ተንከባክቦ በማሳደግ ለውጤት ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በማገዝ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር በመሳተፍ አሻራቸውን ለማኖር ዝግጁነታቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪክ ዲሞክራትክ ፓርቶ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ወንድሙ ኡቶ ናቸው።
ችግኝ መትከል አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ ብዝሃ ሕይወትን በመንከባከብ ሰውና ተፈጥሮን የማስተሳሰር ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ጠቁመው፣ "በነገውም እለትም የፓርቲ አባላትን በማስተባበር ጭምር በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ በመሳተፍ የበኩሌን እወጣለሁ" ብለዋል።
የጌዴኦ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ተወካይ አቶ ተመስገን ፈይሳ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ሥራ ለትውልድ የሚሸጋገር ተግባር በመሆኑ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የጌዴኦ ህዝብ ዛፍን መትከል፣ ደንን መንከባከብና የአፈር ለምነትን መጠበቅ የኑሮ መሰረቱ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ባህል አጠናክሮ ለማስቀጠል የፓርቲው አባላት በነገው የችግኝ ተከላ መርሀግብር በነቂስ እንዲሳተፉ አስገንዝበዋል።
እሳቸውም በችግኝ ተከላ መርሀግበሩ ንቁ ተሳታፊ በመሆን በዞኑ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።