የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ለማሳካት ዝግጅት አጠናቀናል- በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ለማሳካት ዝግጅት አጠናቀናል- በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች
ድሬዳዋ ፤ነሐሴ ፤16 /2016 (ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ አስተዳደር የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላን ለማሳካት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ።
በድሬዳዋ አራቱ የገጠር ክላስተሮች አንዱ በሆነው የቀላድ ክላስተር ነዋሪዎች የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ለማሳካት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በቀላድ ክላስተር ከሚገኙ ስምንት ገጠር ቀበሌዎች የነገው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ የሚጀመርበት የለገ ዲኑ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር መሐመድ ከዲር እንደተናገሩት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ መትከልና መንከባከብ እንዲሁም የተፋሰስ ልማት ውጤቶችን በሚገባ የተረዳ ማህበረሰብ ተገንብቷል።
“የአረንጓዴ አሻራ በአካባቢያችን ከፊል አርሶአደሮች ለእንስሳት አስፈላጊውን ውሃ እና የግጦሽ ሳር በቀላሉ ማግኘት ያስቻለ በመሆኑ የነገውን የችግኝ ተከላ ለማሳካት ዝግጅት አጠናቀናል” ብለዋል።
ወይዘሪት መፍቱሃ አሚን በበኩላቸው “በአረንጓዴ አሻራ ተጠቃሚነታችን እየተረጋገጠ በመምጣቱ በነገው እለት ችግኝ ለመትከል ዝግጅታችንን አጠናቀናል” ብለዋል።
ባለፉት አመታት በተከልናቸው ችግኞች " የምንጭ ውሃ ጎልብቷል፣ ፍራፍሬ ማምረት ጀምረናል፣ በረሃ የነበረው ደረቅ አየር ተለውጧል፣ያሉት ወይዘሪት መፍቱሃ ተሳትፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል ።
“የቀላድ አየር በዚህ መንገድ ቀዝቅዞና ለእንሰሳት ምግብ አብቅሎ አያውቅም” ያሉት ደግሞ አርሶአደር መሐመድ ሁሶ ናቸው።
“የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ውብ አካባቢ ለማየት ያስቻለ በመሆኑ ለልጆቼ የተሻለ አካባቢ ለመፍጠር ነገ የደን እና የፍራፍሬ ችግኞች ተክዬ እንከባከባለሁ” ብለዋል።
የቀላድ ክላስተር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኒአሚን መሐመድ በበኩላቸው በክላስተሩ በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች በአንድ ጀንበር ነገ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች ለመትከል ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸዋል ።
“ከዚህ ቀደም የተተከሉት ችግኞች በቅለው የጎርፍ አደጋን ከመከላከል ባሻገር የጠፉ ምንጮች ጎልበትው አርብቶአደሮች በቀላሉ ለከብቶቻቸው በቂ ውሃ ማግኘት አስችሏቸዋል” ብለዋል።
የነገውን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ለማሳካት የቀላድ ክላስተር ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው የማስጀመሪያውን አካባቢ እያስተካከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ፤ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ኃላፊና የክላስተር የአረንጓዴ አሻራ አስተባባሪ አቶ ፉአድ መሐሙድ በድሬዳዋ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላን ለማሳካት አራቱ የገጠር ክላስተር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀው የተከላውን መርሃግብር እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።