ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ በፍትሐ-ብሔር ክርክሮች 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ማዳኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 16 /2016 (ኢዜአ)፦ቢሮው በተጠናቀቀው  በጀት ዓመት በፍትሐ-ብሔር  ክርክሮች  5 ነጥብ 2 ቢሊዮን  ብር የሚገመት ገንዘብ ማዳን መቻሉን አስታውቋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት ዕውቅና መሰጠቱ ይታወቃል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ዕውቅናው ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል  አንዱ ነው።

ቢሮው " የተሰጠን ዕውቅና ለሌላ ተጨማሪ ድል እንድንተጋ ያደርገናል " በሚል ሃሳብ ለሰራተኞቹና ለአስራ አንዱ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽህፈት ቤቶች የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።  


 

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ቢሮው የከተማ አስተዳደሩን ተቋማት በመወከል የህዝብና የመንግስትን መብት የሚያስከበሩ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማሳለጥ የሚያስችሉ የህግ፣ የአሰራርና የአደረጃጀት ማዕቀፎች በማዘጋጀት እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ክርክር ከተደረገባቸው 8 ሺህ 514 የፍትሐ-ብሔር መዝገቦች ውስጥ  5 ሺህ 352 መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።

ቢሮው ክርክር ከተካሄደባቸው መዝገቦች ውስጥ 5 ሺህ 44 ክሶችን መርታት መቻሉን በማስታወቅ 308 መዝገቦች ለመጪው ዓመት መቀጠራቸውን ተናግረዋል።

ይህም  የቢሮውን ክስ የመርታት አቅም መጎልበት እንደሚያሳይ አስታውቀዋል።  

ክርክር የተካሄደባቸው ጉዳዮች መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ህንጻ፣ ኮንደሚኒየም ቤቶች ፣ ሼዶች  እና የመሬት ጉዳዮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ቢሮው በክርክር ያሸነፈባቸው የክስ መዝገቦች በገንዘብ ሲተመኑ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንደሚጠጉ አብራርተዋል።

ነጻ የህግ አገልግሎት ድጋፍ ለጠየቁ አቅመ ደካማ የከተማዋ ነዋሪዎች ድጋፍ መደረጉንና ለ 1 ሺህ 475  የህግ ምክር ፈላጊዎች ነጻ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በደንብ መተላለፍ  ከቀረቡት መዝገቦች ውስጥ 206ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን አክለዋል።

በመድረኩም የ2016 በጀት ዓመት የቢሮውን ዕቅድ አፈጻጸም የያዘ ዝርዝር ሪፖርት ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ቢሮው ባለፈው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሰራተኞችና ክፍለ ከተሞች ዕውቅና ሰጥቷል።

በቢሮው በሰው መነገድና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል መከላከል ማስተባበሪያ ዐቃቤ ህግ የሆኑት ወይዘሮ መኪያ ዲኖ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ወይዘሮ መኪያ ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ፈጠራና ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ በሰሩት ስራ ለሽልማት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

በክፍለ ከተማ ደረጃ አቃቂ ቃሊቲ የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ ቀዳሚ በመሆን ዕውቅና ተሰጥቶታል። 

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስናቀ ረታ በበኩላቸው የተሰጣቸው ዕውቅና በቀጣይ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚያነሳሳቸው አስታውቀዋል።

ጽህፈት ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለአቅመ ደካሞች ነጻ የህግ ድጋፍ በመስጠት፣ በህግ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የመንግስትና የህዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ ተግባራትን በማከናወንና የህግ ተፈጻሚነትን በማረጋገጥ አመርቂ ተግባር ማከናወኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም