የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የልማት ክንውኖችን በማሳደግና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻል የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የልማት ክንውኖችን በማሳደግና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻል የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የልማት ክንውኖችን በማሳደግና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻል የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ጋር በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የታክስ ንቅናቄ በሚመለከት ውይይት አድርጓል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ መምሪያ ኃላፊ ሙላይ ወልዱ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግብር ከፋዩና ለዜጎች ያለውን ጠቀሜታ በመዘርዘር ተወዳዳሪና ዘመናዊ የምጣኔ ኃብት እድገት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
የገቢ መሰብሰብ አቅምን በማሳደግ ልማትና ፋይናንስን በሀገር ውስጥ አቅም መሸፈን የማሻሻያው ትኩረት መሆኑን፤ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ፈጣንና ፍትሃዊ እድገት እንዲሁም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካትና ፍትሃዊ የውድድር አውድ ለመፍጠርም የገቢ ምንጭን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መስከረም ደበበ፤ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እያደገ ቢመጣም ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው አንጻር የሚሰበሰበው ገቢ አሁንም በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
በግብር ከፋዩ ዘንድ በአብዛኛው ግብርን በወቅቱና በታማኝነት አሳውቆ ያለመክፈል፣ የአሠራር አለመዘመን፣ የሰው ኃይል ብቃትና የስነ-ምግባር ችግር በምክንያትነት ከሚነሱት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ሚኒስቴሩ እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመፍታት የተሻለ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከተገኙ አነስተኛ ግብር ከፋዮች በሰጡት አስተያየት በግብር አከፋፈል ሂደቱ መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን የአሠራር ችግሮች አንስተዋል።
በውይይቱ የምዕራብ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 የገቢ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ 12 ሺህ 800 ግብር ከፋዮች እንዳሉትም ተገልጿል።