በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በጭጋጋማ አየር ምክንያት አብዛኛዎቹ በረራዎች በአቅራቢያ ወደሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲዛወሩ መደረጉን አየር መንገዱ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በጭጋጋማ አየር ምክንያት አብዛኛዎቹ በረራዎች በአቅራቢያ ወደሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲዛወሩ መደረጉን አየር መንገዱ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2016(ኢዜአ)፦በጭጋጋማ አየር ምክንያት በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደረጉ አብዛኛዎቹ በረራዎች በአቅራቢያ ወደሚገኙ ሌሎች አማራጭ አውሮፕላን ማረፊያዎች መዛወራቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
አየር መንገዱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ ዛሬ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ በተከሰተው ጭጋጋማ የአየር ጸባይ ምክንያት አብዛኛዎቹ በረራዎች በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም ፡፡
ይህ የአየር ሁኔታ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም-አቀፍ የጠዋት በረራዎቻችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ያለው አየር መንገዱ የመንገደኞች ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በተሳፋሪዎቻችን የጉዞ ዕቅዶች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ መስተጓጉሎችን ለመቅረፍ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረግን እንገኛለን ሲልም አስታውቋል።
በመዲናዋ በተፈጠረው አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ምክንያት በመንገደኞች ላይ ለደረሰው መጉላላትም አየር መንገዱ ይቅርታ ጠይቋል፡፡