የፖሊስን የሕክምና ተቋማት በሁሉም መልኩ በማደራጀት ለሠራዊቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው- ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊስን የሕክምና ተቋማት በሁሉም መልኩ በማደራጀት ለሠራዊቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው- ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ ፤16 /2016 (ኢዜአ)፦የፖሊስ የሕክምና ተቋማትን በባለሙያ፣ በግብዓትና ቴክኖሎጂ በማደራጀት ለሠራዊቱና ቤተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሰው ኃብት አስተዳደር ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ ገለጹ።
የፌደራል ፖሊሲን የሪፎርም ሥራዎችና አጠቃላይ ዝግጁነት በተመለከተ ኢዜአ ከምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኘ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ በማብራሪያቸው ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በፀጥታ ተቋማት ላይ በተደረገው የሪፎርም ሥራ ፌደራል ፖሊስ ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በብዙ መልኩ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰው፤ በተለይም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ሰው ኃይል ልማትና በሌሎችም ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
በጤና እና በአካል ብቃት ጠንካራና ብቁ የፖሊስ ኃይል በማፍራት ለሀገርና ሕዝብ አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት የፖሊስን የሕክምና ተቋማት በባለሙያ፣ በግብዓትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ተችሏል ብለዋል።
የፖሊስን የሕክምና ተቋማት ለማስፋት በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ስኬት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የተሟላ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ለሀገርና ሕዝብ አስተማማኝ አገልግሎት የሚሰጥ የፖሊስ ኃይል እየተገነባ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ የፖሊስ የሕክምና መስጫ ተቋማት ለሠራዊቱና ለቤተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ገልፀዋል።
በሪፎርሙ የፖሊስ ብቃትና አገልግሎትን መሠረት በማድረግ የብሔር ብሔረሰቦችን ተዋጽዖ ታሳቢ ያደረገ የተሟላና ጠንካራ አደረጃጀት መፈጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከ51 ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም የፖሊስ አባላቱ ከ71 ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሪፎርሙ የሴቶችን ተሳትፎ በአመራርና በአባል ደረጃ በማሳደግ የተሳካ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ ትግበራና የሰው ኃይል ልማት በውጭና በሀገር ውስጥ ትምህርትና ሥልጠና በስፋት በመስጠት የማብቃት ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።
በወንጀል መከላከልና በምርመራ ዘርፍም አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የፖሊስን ሥራ ፈጣንና የተቀላጠፈ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በወንጀል መከላከልና በመረጃ አሰባሰብ የፖሊስን ብቃት ከማሳደግ ባለፈ የድሮን፣ የሞባይል መተግበሪያ፣ የሲሲቲቪ (በደኅንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች) እና ሌሎችም ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑ ይታወቃል።