በአማራ ክልል ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 16/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ነገ በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅትና ችግኝ የማጓጓዝ ተግባር ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በግብርና ቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፤ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲደረግ የቆየው ዝግጅት ተጠናቋል።
በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው ችግኝ ተከላም 28 ሺህ 500 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮ ስራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
ለተከላ የተዘጋጁት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችንም በሁሉም የክልሉ አካባቢ ወደ ተዘጋጁ የመትከያ ቦታዎች የማጓጓዙ ስራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ወይራ፣ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ ፅድ፣ ግራር፤ ከፍራፍሬ ደግሞ አቦካዶና ማንጎን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ስለተከላው በቴክኖሎጂ ታግዘው መረጃ የሚሰጡ ከ2 ሺህ 700 በላይ ባለሙያዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል።
ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ላይ ከ5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው ፤ "አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን፤ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ ዓሻራችንን እናኑር" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኞች በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ማለታቸው ይታወቃል።